የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ከህወሓት ጋር ስለሚደረገው ድርድርና ስለ ህዳሴ ግድብ ለመነገጋገር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ
ማይክ ሀመር በአዲስ አበባ ቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት ጋርም የሚመክሩ ይሆናል
ልዩ መልእከተኛው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ግብጽና እና አረብ ኢሚሬትስ ያቀናሉ
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በዛሬው እለት አዲስ አበባ ይገባሉ።
ማይክ ሀመር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ይደረጋል የተባለውን የሰላም ድርድር ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት የመገምገም ዕድል እንደሚኖራቸውም ነው የተገለጸው።
- አምባሳደር ስለሺ በቀለ፤ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር በድርድርና በአጎአ ዙሪያ መወያየታቸው ተገለፀ
- አሜሪካ ማይክ ሀመርን በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ሾመች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን ባወጣው መገልጫ፤ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ያለበትን ሁኔታ መገምገም እንዲሁም በጦርነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ማድረግን የተመከቱ ጉዳዮች ማይክ ሀመር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከሚመክሩባቸው አንኳር ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሷል።
ልዩ መልዕክተኛው ከጦርነቱ በተጨማሪ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብም ይነጋገራሉ ተብሏል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሚወዛገቡበት ጉዳይ ላይ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማምጣት የአሜሪካ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጫው የጠቀሰ ሲሆን ይህም የሁሉንም አካላት ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ነው ተብሏል።
ማይክ ሀመር በአዲስ አበባ ቆይታቸው የሶስትዮሹን ድርድር ሲመራ ከነበረው የአፍሪካ ህብረት ጋርም የሚመክሩ ይሆናል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደሚያቀኑም ነው የተገለጸው።
ዴቪድ ሳተርፊልድን በመተካት በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ማይክ ሀመር ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ሲያደርጉ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና ብልጽግና ለማምጣት ያስችል ዘንድ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደትን መደገፍ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ለማራመድ ቁርጠኛ ነች” ነች ብሏል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት የተለያዩ አሳዛኝ ክስተቶች እያስተናገደና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዋና አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።አሁን ላይ የጦርነቱ ተዋናዮች ማለትም የፌዴራል መንግስት እና ህወሐት ወደ የድርድር ሃሳብ መምጣታቸው የሚታወቅ ነው።
በፌዴራል መንግስት እና ህወሐት መካከል ያለውን ቀውስ በሰለማዊ መንገድ የሚፈታበት መንገድ ካለ፤ አሳዘኝ ውድመት ያስከተለውንና በርካቶችን ለሞትና እንግልት የዳራገውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሰሞኑ የህወሐት ተደራዳሪ ቡዱን ማዋቀሩን በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ በኩል ያስታወቀው ህወሐት በኬንያ መንግስት አሸማጋይነት በናይሮቢ የሚደረግ የሰላም ንግግር ካለ በድርድሩ የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የፌዴራል መንግስት በበኩሉ የሀገር ብሄራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄድ ድርድር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑና ስራ መጀመንሩ፤ በጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ እንዲሁም በሌሎች ባለስልጣናት አማካኝነት ሲገልጽ ቆይቷል።
ሁለቱ አካላት ለሰላም ድርድሩ ያላቸውን ፍላጎት ቢገልጹም ውይይቱ መቼ ይጀመር፣ የትስ ቦታ ነው በሚለው ላይ በግልጽ የተባለ ነገር የለም።