የአማራ ክልል መንግስት በትጥቅ ትግል ውስጥ ለሚገኙ አካላት የሰላም ጥሪ አቀረበ
በክልሉ በየትኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀት የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሰባት ቀናት ውስጥ ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ነው ጥሪ የቀረበው
የክልሉ መንግስት የሰላም ጥሪውን በማይቀበሉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል
የአማራ ክልል መንግሥት “በክልሉ ግጭት እንዲያበቃና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን” የሰላም ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ መንግስት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፥ በክልሉ እየተሻሻለ የመጠውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት የሰላም ጥሪውን ማቅረብ አስፈልጓል ብሏል።
ተጨማሪ ደም መፋሰስን፣ ጥፋትን እና ውድመትን ለማስቀረት በማሰብ ለታጣቁ ሃይሎች የሰላም ጥሪ ማቅረቡንም አስታውቋል።
“የፖለቲካ አጀንዳ እና ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኙ በፅኑ በማመን እና ለሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት እና ምክክር መንገድ የሚጠርግ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ በመሆኑ” የሰላም ጥሪው መቅረቡንም ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በመሆኑም በክልሉ በየትኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀትና ትጥቅ ትግል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሰባት ቀናት ውስጥ ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ነው ጥሪ ያቀረበው።
“ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ በሚገኙ የኮማንድ ፖስት አዛዦች ለዚሁ አላማ ለይተው ለሕዝብ ወደሚያሳውቋቸው የመሰብሰቢያ ስፍራዎች በመሄድ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲያሳውቁ”ም ጠይቋል።
ወደ ሰላማዊ ኑሮ የሚመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሃድሶ ማዕከላት ውስጥ አስፈላጊውን ሥልጠና እንዲያገኙ ይደረጋልም ብሏል መግለጫው።
በተሃድሶ ማዕከላት ስልጠና ተሰጥቷቸው የሚወጡ ታጣቂዎች በግጭት ወቅት በምህረት ሊሸፈኑ የሚችሉ ወንጀሎች ከፈጸሙ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ እንዲሆኑ እንደሚደረግም ነው የተጠቀሰው።
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም ለሰላም ጥሪው መሳካት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል።
የሰላም ጥሪውን በማይቀበሉ የታጠቁ ሃይሎች ላይ የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ ተጥናክሮ ይቀጥላል ሲልም ነው የአማራ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
የፌደራል መንግሰት የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ ከወሰነበት ከባለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር አጋጥሞታል።
የጸጥታ ችግሩን በመደበኛ የህግ ማስከበር ስራ መቆጣጠር እንደማይቻል የገለጸው መንግስት በክልሉ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ፣ በታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቁን መግለጹ ይታወሳል።
የክልሉ እና የፌደራል መንግስታት በተከታታይ በሰጡት መግለጫቸው አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሱን ሲገልጽ ቆይቷል።
ነገርግን በታጣቂዎቹ እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ከትላልቅ ከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች ውጊያዎች መቀጠላቸውን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
በውጊያው አውድም የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የሰብዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ በፊት ባወጣው ሪፖርት ማቅረቡ ይያወሳል።