“ምዕራባውያን ከሩሲያ ጋር መጫወታችሁን አቁሙ፤ ጦርነት ይብቃ ”- ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ
ዘሌንስኪ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ለመጣል “በአውሮፓ ህብርት ውስጥ ያለው ልዩነት” በጣም እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል
ፕሬዝዳንቱ “ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ሊጥሉ ይገባል” ሲሉም ጠይቋል
በዩክሬን እየተካሄደ ያለው "ትርጉም-አልባ ጦርነት" እንዲያበቃ ምእራባውያን ከሩሲያ ጋር የገቡትን አላስፈላጊ ጨዋታ ሊያቆሙ ይገባል ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሜር ዘሌንስኪ አሳሰቡ፡፡
በምዕባውያን ላይ ያነጣጠረው የዘሌንስኪ ትችት የመጣው፤ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ለመጣል በጣም ዘገምተኛ መሆኑን እንዲሁም የሩሲያ ኃይሎች ሴቪየርዶኔትስክ እና ሊይሲቻንስክ የተባሉ የዩክሬን ቁልፍ ከተሞችን በከበባ ውስጥ ለማስገባት መጠነ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የምዕራቡ ዓለም የወታደራዊ ሳይንስ ልሂቃን እንደሚሉት፤ በሴቪየርዶኔትስክ እና ሊይሲቻንስክ የሚደረግ ጦርነት ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከወደቀችው ማሪዩፖል ከተማ ቀጥሎ የሚደረግና በጦርነቱ ምናልባትም የሩሲያ የበላይነት የሚታይበት ሊሆን የሚችል ነው፡፡
በዚህም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገቡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ፤ ምዕራባውያን ከሩሲያ ጋር የጀመሩት ጨዋታ አቁመው የሚታይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ “ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ሊጥሉ ይገባል” ሲሉም ጠይቋል፡፡
"ዩክሬን ሁል ጊዜ ነፃ ሀገር ትሆናለች ፣አትፈርስም፡፡ ጥያቄው ዩክሬናውያን ለነፃነታቸው ምን ያህል ዋጋ መክፈል አለባቸው እንዲሁም ሩሲያ ለዚህ ትርጉም የለሽ ጦርነት ምን ያክል ዋጋ ትከፍላለች የሚለው ነው ….?" ሲሉም አክሏል ዘሌንስኪ::
ዘሌንስኪ ትናንት ምሽት ባደረጉት ንግግር፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሁም ኃያላን ሀገራት በዩክሬን ያለውን ሁኔታ በተለመደ መልኩ በጥንቃቄ ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ፤ አሁን እየተከሰቱ ያሉ አስከፊ ክስተቶች ሊቆሙ ይችሉ ነበር የሚል ጸጸት አዘል መልእክትም አስተላልፈዋል፡፡
ዘሌንስኪ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል በሚያስችል አጀንዳ ላይ ስላለው አለመግባባት ያላቸው ቅሬታም ሰንዝሯል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ ነዳጅ ወደ አውሮፓ ምድር እንዳይገባ ለማድረግ የሚያስችል እገዳን ጨምሮ ስለ ስድስተኛ ዙር የቅጣት እርምጃዎች እየተወያየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ አውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ሊያኖረው የፈለገውን ማእቀብ እውን እንዳይሆን ፤ማዕቀቡ ከተጣለ ኢኮኖሚዋ ኩፉኛ እንዳይጎዳ የምትሰጋው ሃንጋሪ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳሰማች ተገልጿል፡፡
ዘሌንስኪ በትናንቱ ንግግራቸው "የአውሮፓ ህብረት በስድስተኛው እርምጃ ላይ ለመስማማት ስንት ተጨማሪ ሳምንታት ይወስድበት ይሆን?" ሲሉ ጠይቋል፡፡
በሩሲያ ላይ ያለው ጫና በጥሬው ህይወትን የማዳን ጉዳይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ፤ በየእለቱ በሚታዩ የመዘግየት፣ የድክመት እና የተለያዩ አለመግባባቶች ዩክሬናውያን ህይወት እያስከፈሉ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።