ሱዳን በአልፋሽቃ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ሰበሰብኩ አለች
ሱዳን ከአልፋሽቃ ምርት የሰበሰብኩት ከ25 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብላለች
በኢትዮጵያ ግዛት ስር የነበረው አልፋሽቃ ባሳለፍነው ዓመት በሱዳን ወረራ መያዙ ይታወሳል
ሱዳን ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአልፋሽቃ ከ142 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተዘራ ሰብል መስበሰብ መቻሏን አስታወቀች።
በምስራቅ ሱዳን የሚገኘው የገዳሪፍ ክልል የግብርና ቢሮ ተጠባባቂ ሚኒስትር አህመድ ሃሳ አሎባ በሰጡት መግለጫ፤ “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት አልፋሽቃ ስኬታማ የግብርና ስራ አከናውናለች” ብለዋል።
- ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት የአል ፋሽቃ የድንበር አካባቢ የገነባቻቸውን መሰረተ ልማቶች አስመረቀች
- ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ግጭት ውስጥ ቢገቡም የድንበር ላይ ንግዱ አልተቋረጠም-የአካባቢው ባለስልጣን
“በአሁኑ የእርሻ ወቅት በአልፋሽቃ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር አልነበረም” ያሉት አህመድ ሃሳ አሎባ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የድንበር ውዝግብ ምክንያት የእርሻ ስራው የፀጥታ ስጋት ባለባቸው ስፍራዎች በሀገሪቱ ታጣቂ ሀይሎች መከናወኑንም አስታውቀዋል።
በዘንድሮው የእርሻ ወቅትም በአልፋሽቃ በ142 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ በተከናወነው ስራ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ እና ማሽላ በስፋት መመረቱን ያስታወቁት ተጠባባቂ ሚኒስትሩ፤ የሱፍ አበባን ጨምሮ ሌሎችም የቅባት እህሎች መሰብሰባቸውን ገልፀዋል።
ገዳሪፍ ከፍተኛ ዝናብን ከሚያገኙ እና ምርታማ ከሆኑ የሱዳን አካባቢዎች ቀዳሚ እንደሆነ ይነገራል።
ኢትዮጵያ “ሉዓላዊ መሬቴ ነው” የምትለው አልፋሽቃ በአሁኑ ወቅት በገዳሪፍ ክልል ስር ይገኛል፡፡ ካሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት ወዲህም የሱዳን ጦር የተለያዩ የአል ፋሽቃ አካባቢዎችን “ወርሮ” ይዟል፡፡
አልፋሽቃ ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ግዛት ስር የነበረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የተለያዩ የእርሻ ስራዎችን ሲያከናውኑበት ነበረ።
ኢትዮጵያ የሱዳን ጦር ከያዛቸው ሉዓላዊ የኢትዮጵያ መሬቶች ለቆ እንዲወጣ እና ከአሁን ቀደም የተጀመሩ ድርድሮች እንዲቀጥሉ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ድልድይና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መገንባቱን እንዲያቆም ጭምር አሳስባ እንደነበር መገለጹም የሚታወስ ነው።