በጦርነት ሰቆቃ ውስት ያሉ ወገኖቻችን ማስደሰት እንፈልጋለን - የሱዳን ተጫዋቾች
የአፍሪካ ዋንጫ መስራቿ ሀገር በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሞሪታንያን ትገጥማለች
ሱዳን በጦርነቱ ምክንያት በሜዳዋ ማድረግ የነበረባትን ጨዋታ በሞሮኮ ታካሂዳለች
የሱዳን ተጫዋቾች በጦርነት ውስጥ ለሚገኘው ወገናቸው ደስታ እና ተስፋን ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ሱዳን ዛሬ በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሞሪታንያን ትገጥማለች።
ምሽት 4 ስአት የሚደረገው ጨዋታ በሱዳን ሜዳ የሚደረግ ቢሆንም ሁለት ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ምክንያት በሞሮኮ ሊደረግ ግድ ሆኗል።
በምድብ 9 ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋቦን እና ሞሪታንያ ጋር የተደለደለችው ሱዳን አራት ጨዋታዎችን አድርጋ በ6 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ዛሬ በአድራር ስታዲየም የምታደርገውን ጨዋታ ካሸነፈች በ9 ነጥብ ምድቡን መምራት ትጀምራለች።
ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የምታደገውን የመጨረሻ ግጥሚያ ማሸነፍ አልያም አቻ መለያየት ኮቲዲቯር በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን እንድታረጋግጥ ያደርጋታል።
“ከሀገራችን ከስታዲየማችን መራቅ ይከብዳል፤ ነገር ግን ሁላችንም የቡድኑ አባላት ጨዋታውን አሸንፈን ለወገኖቻችን ደስታ ለመስጠት ተዘጋጅተናል” ብሏል አማካዩ ሙታዝ ሃሻም።
በአድራር ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ “ሱዳናውያንን አንድ የሚያደርግና የሁለት ወራት ሰቆቃቸውን ለተወሰኑ ቀናትም ቢሆን የሚያስረሳ እንዲሆን ሁላችንም በሜዳ ላይ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል”ም ነው ያለው ተጫዋቹ።
የአፍሪካ ዋንጫ መስራቿ እና የ1970ውን ዋንጫ ያነሳችው ሱዳን የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታዋን በመስከረም ወር ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ታደርጋለች።