ኢትዮጵያ፤ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት ውሳኔን እንደምታከብር ገለጸች
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሀን ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ስለመባሉ ይፋዊ መረጃ የለም ተብሏል
የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት መሪነት መካሄዱ ይቀጥላልም ብላለች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው በሱዳን በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሱዳናውያን ያለማንም ጣልቃ ገብ ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩ እንዲሁም ችግራቸውን ሲፈቱ ማየት የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው ብለዋል።
ከአፍሪካ ህብረት የታገደችው ሱዳን በግድቡ የድርድር ሂደት አትሳተፍም ተባለ
የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደምትደግፍ የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ ሱዳናውያን የጀመሩትን የዲሞክራሲ ሽግግር እንደሚቀጥሉበት ተስፋ ማድረጋቸውንም አክለዋል።
ከህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ሶስት ሃገራት መካከል አንዷ ሱዳን አንዷ ናት። ሆኖም በመፈንቅለ መንግስቱ ምክንያት ከየትኛውም የአፍሪካ ህብረት የስራ እንቅስቃሴዎች ታግዳለች።
ይህ መሆኑ ድርድሩን ይጎዳው ይሆን ወይ? በሚል የተጠየቁት አምባሳደሩ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ውሳኔን ታከብራለች፤ የሶስትዮሽ ድርድሩም ከአፍሪካ ህብረት ውጭ እንዲካሄድ አትፈልግም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሶስትዮሽ ድርድሩ ዙሪያ የምታቀርበውን የድርድር ፕሮግራም እየጠበቁ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ዲና ሁኔታው በቀጣይ ይገለጻልም ብለዋል።
ሌ/ጄ አል-ቡርሃን በአሜሪካና አውሮፓ ህብረት የሚገኙትን ጨምሮ 6 የሱዳን አምባሳደሮችን ከስራ አባረሩ
በሃገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ውይይት እንደሚደረግ ከአሁን ቀደም ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ በውይይቱ ማን ሊሳተፍ እንደሚችል የተጠየቁት ቃል አቀባዩ “እነማን ይሳተፋሉ የታጠቀ ያልታጠቀ በሚለው ዙሪያ አዲስ የተመረጠው መንግስት እየመከረበት ነው በቅርቡ ያሳውቃል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
“የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሀን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው” የሚሉ የተለያዩ መረጃዎች ከሰሞኑ በየማህበራዊ ሚዲያው ሲሰራጩ ነበር፡፡
ስለ መረጃዎቹ የተጠየቁት ዲና “ይፋዊ መረጃ የለኝም” ብለዋል።
ባለፉት ቀናት በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ 433 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።