የሀገሪቱ ጦር መሪ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄ/ል መሃመድ ዑስማን አልሁሴን ግን ከስልጣናቸው አልተነሱም
ሱዳን ወታደራዊ ሹም ሽር አደረገች፡፡
ወታደራዊ ሹም ሽሩ በጊዜያዊው ወታደራዊ መሪው ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የተደረገ ነው፡፡
ከአሁን ቀደም አዲስ የአየር ኃይል ወታደራዊ አመራሮችን የሾሙት ቡርሃን የምድር ጦርን ጨምሮ በዘመቻ መምሪያ እና በወታደራዊ ሎጂስቲክ መምሪያዎች ሹም ሽር አድርገዋል፡፡
በሹም ሽሩ መሰረትም ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለአስተዳደር ሌተናል ጄኔራል ሙናዋር ኦስማን ኑቁድ እና ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለስልጠና ሌተናል ጄኔራል አብዱላህ አልበሽር አህመድ አል-ሳዲቅ የአንደኛ ሌተናል ጄኔራልነት ማዕረግን አግኝተው በጡረታ ከጦሩ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡
የምድር ጦር አዛዡ ሌተናል ጄኔራል ኢሳም መሃመድ ሐሰን ከራር እንዲሁም የሌተናል ጄኔራልነት ማዕረግን ያገኙት ሜጀር ጄነራል አህመድ ዑመር ሸናን በተመሳሳይ መልኩ ጡረታ ወጥተዋል፡፡ ሌሎች የሌተናል ጄኔራልነት የማዕረግ እድገቶችና ሹመቶችም ተሰጥተዋል፡፡
በዚህም ሜጀር ጄነራል አብዱል ሃሚድ ኢስማይል ሌተናል ጄኔራል ተብለው በምድር ጦር አዛዥነት ተሾመዋል እንደ ሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዘገባ፡፡
ሜ/ጄ አብዱል ማህሙድ ሃማድ ሁሴን አጃሚ፣ ሜ/ጄ ናስር አል-ዲን አብዱል ቀይዩም አህመድ አሊ እና ሜ/ጄ ሙባረክ ኮቲ ካጁር ክምቶር ደግሞ የጦር ኃይሎች ዋና ኢንስፔክተር ሆነው በቡርሃን ተሾመዋል።
የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ጦሩን በአዲስ መልኩ ለማደራጀት ያስችላሉ ያሏቸውን ሌሎች ሹም ሽሮችንም አድርገዋል፡፡ ሆኖም ቡርሃን የሃገሪቱን ጦር ኃይሎች መሪ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄ/ል መሃመድ ዑስማን አልሁሴንን ከስልጣናቸው አላነሱም፡፡
ሹም ሽሩ ቡርሃን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መንግስትን አስወግደው ስልጣን ከያዙበት ካሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት ወዲህ የተደረገ ወታደራዊ እርምጃ ነው፡፡ በወቅቱ የሃገሪቱን ጦር በአዲስ ማደራጀታቸውና የተለያዩ ሹመቶችን መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ቡርሃን የሱዳንን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት በፕሬዝዳንትነት እንደሚመሩ ይታወቃል፡፡