በቅርቡ ግብፅን የጎበኙት የሱዳኑ አልቡርሃን ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሏል
አልቡርሃን በቀጣናዊ ለውጦች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል
ሁለቱ መሪዎች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያም ሊመክሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል
ሁለቱ መሪዎች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያም ሊመክሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል
ከሰሞኑ በካይሮ ጉብንት አድርገው የነበሩት የሱዳን የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ነገ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለአል ዐይን ኒውስ እንደገለጹት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡ በቀጣናዊ ለውጦች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል፡፡
አዲስ አበባና ካርቱም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡
አልቡርሃን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ግድብ ላይ ከሰጡትና ኢትዮጵያውያንን ካስቆጣው አስተያየታቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የመጀመሪያ መሪ ያደርጋቸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ አል ቡርሃን ከግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በዚህ ወቅት ካይሮ እና ካርቱም የሕዳሴ ግድብን ሙሌት እና አሰራሩን አስመልክቶ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
የሱዳን የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) ሰኔ 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡