ሱዳን፤ አስገዳጅ ሁኔታ እስካልገጠማቸው ድረስ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣት እንዲዘጋጁ አሳሰበች
ተጨማሪ 500 ሺ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳሰበችው ሱዳን በገዳሪፍ ግዛት ሁለት ተጨማሪ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ስለማቀዷ አስታውቃለች
ካርቱም ዜጎቿ ከአዲስ አበባ ውጭ እንዳይጓዙ አስጠንቅቃለች
አስገዳጅ ሁኔታ እስካልገጠማቸው ድረስ ዜጎቿ በፈቃደኝነት ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ሱዳን አስጠነቀቀች፡፡
ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታዎችን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው በኢትዮጵያ የሱዳን ኤምባሲ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙ ሱዳናውያን እንዲጠነቀቁ አሳስቧል፡፡
በምትንቀሳቀሱበትም ሆነ በየትኛውም አጋጣሚ ማንነታችሁን የሚገልጽ መታወቂያ መያዛችሁን እንዳትረሱ ሲል ዜጎቹን ያሳሰበው ኤምባሲው ከመሰባሰቦች እንዲርቁ እና ከአዲስ አበባ ውጪ እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን በማስታወስም አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልገጠሟቸው በስተቀር ሱዳናውያኑ ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣት የሚያስችላቸውን አስፈላጊውን የበረራ ዝግጅት በፈቃደኝነት እንዲያደርጉም አስጠንቅቋል ኤምባሲው፡፡
ኤምባሲው በማሳሰቢያው ላይ ለውጦችን ሊያደርግ እንደሚችል እና በኢትዮጵያ የሱዳን ዜጎችን ደህንነትና ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቋል።
የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት የተጀመረው ድርድር “ግማሽ መንገድ ላይ ቆሟል”ተባለ
በተያያዘ ሌላ ተጨማሪ ዜና ሱዳን በገዳሪፍ ግዛት ሁለት ተጨማሪ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ስለማቀዷ አስታውቃለች፡፡
መጠለያዎቹ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ያለቻቸውን ተጨማሪ 500 ሺ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ለመቀበል የሚያስችሉ ናቸው እንደ ሃገሪቱ ዜና አገልግሎት (ሱና) ዘገባ፡፡
ሱና መጠለያ ጣቢያዎቹን ለመገንባት የገዳሪፍ ግዛት አስተዳደር ተስማምቷል ሲልም ነው የዘገበው፡፡ መጠለያዎቹ በአል ፋኦ እና አል ሶውኪ የሚገነቡ ናቸው የግዛቱን የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኃላፊ ዋቢ እንዳደረገው እንደ ሱና ዘገባ፡፡
የሱዳን ጦር መፈንቅለ መንግስቱን ለመቃወም በወጡ መምህራን ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ
ከአሁን ቀደም ወደ ሱዳን አቅንተው ኡም ራኩባ፣ አል ቲናዲባ እና ባሱንዳ በተባሉ መጠለያ ጣቢያዎች የተጠለሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ፡፡
ሆኖም ስደተኞች በትግራዩ ግጭት በተለይም በማይካድራው ጭፍጨፋ የተሳተፉ ናቸው፤ “የስደተኞች መታወቂያ ይዘው ከመጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ሲሳተፉ የተገኙ ታጣቂዎች አሉ” ሲባል ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከአሁን ቀደም ለአል ዐይን አማርኛ መግለጫ የሰጠው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር መቀነሱን በመጠቆም “ስደተኞች የት እንዳሉ ማረጋገጥ አልቻልኩም” ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡