ሱዳናውያን፤ የጎሳ ግጭትና ዘረኝነት እንዲቆም የሚጠይቅ ሰልፍ አደረጉ
በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት በጎሳ ግጭት የተከሰተውን ግድያ የሚያወግዝ ሰልፍ ተደርጓል
በሱዳን በርቲ እና ሀውሳ በተባሉ ጎሳዎች መካከል በተከሰተው ግጭት ከ65 በላይ ሰዎች ተገድለዋል
በሱዳን ብሉናይል ግዛት በተፈጠረ ግጭት ዜጎች በመገደላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ ወደ ካርቱም አደባባይ የወጡት በብሉ ናይል ግዛት በጎሳ ግጭት ምክንያት ከ65 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
በሱዳን ብሉናይል ግዛት በበርቲ እና ሀውሳ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ የጎሳ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ65 በላይ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ሰልፈኞቹ በያዙት መፈክር ገልጸዋል።
በካርቱም የሚገኘው የአል ዐይን ኒውስ ዘጋቢ ባደረሰን መረጃ፤ ሰልፉ በሀውሳ ጎሳዎች አነሳሽነት እንደተጀመረ፤ የጎሳ ግጭት እና ዘረኝነት እንዲቆም ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሷል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች ዘረኝነትና አካባቢዊነት ሊወገዝ እንደሚገባው የጎሳ ግጭቶች መደገም እንደሌለባቸው ገልጸዋልም ተብሏል።
ሰልፈኞቹ በአውሮፕላን ማረፊያውን አካባቢ መድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን የሱዳን የጸጥታ ሰዎችም አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል ተብሏል፡፡
ዛሬ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ሱዳናውያን ከደቡብ ካርቱም ተነስተው ወደ መከላከያው ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ መድረሳቸው ተነግሯል።
የሱዳን ፖሊስ በርካታ ተሳታፊዎች የነበሩበትን ሰልፍ ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ተገልጿል። በርካታ ሰልፈኞች በሱዳን ጦር ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ መሰባሰባቸውን ተከትሎ ጦሩ ወደ ዋናው ማዘዣ የሚወስዱትን መንገዶችን እየዘጋ ነውም ተብሏል።
በሱዳን በተከሰተው የጎሳ ግጭት ምክንያት ከሰዎች መሞትና መጎዳት ባለፈም ከ16 በላይ የንግድ ሱቆችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችም መውደማቸው ተገልጿል።
ብሉናይል ግዛት ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች ያለ የሀገሪቱ ክፍል ሲሆን ከዚህ በፊት መሰል ችግሮች ሲከሰቱበት እንደነበር ይታወሳል።
የጸጥታ ኃይል ወደ ስፍራዎቹ መላኩን ተከትሎ በብሉናይልና በከሰላ አካባቢ ያለው ችግር እየበረደ መሆኑን ሱዳን አስታውቃለች። ምንም እንኳን ችግሩ ቢቃለልም የገዳሪፍ እና ኮስቲ አካባቢዎችም ችግሩ በችግሩ መቆጣታቸው ተሰምቷል።
የግዛቱ ባለስልጣናት በብሉ ናይል ዋና ዋና ከተሞች ለአንድ ወር የሚቆይ የሰዓት እላፊ ቢጥሉም በርካቶች አሁንም ግጭቱ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ተገልጿል።