የሱዳኑ ጄኔራል በደቡብ ዳርፉር ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ አካባቢው ተልዕኮ ይዘው አቀኑ
ከኒያላ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቤሌይል በተባለው አካባቢ በተፈጠረው ሁከት በትንሹ 10 ሰዎች መሞታቸውን እና 25 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል
የአካባቢው መንግስት የሰሞኑ ግጭት በዘላኖች የተፈፀመ ጥቃት ነው ያለ ሲሆን፤ ይህም ሰፊ ጦርነት ቀስቅሷል ብሏል
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ የተቀሰቀሰን አዲስ ግጭት ተከትሎ ባለፈው ሀሙስ ወደ ደቡብ ዳርፉር ኒያላ ከተማ ተልዕኮ በመምራት የጸጥታ ሁኔታውን ገምግመዋል ተብሏል።
ከኒያላ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቤሌይል በተባለው አካባቢ በተፈጠረው ሁከት በትንሹ 10 ሰዎች መሞታቸውን እና 25 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። በግጭቱ በርካታ መንደሮችም መቃጠላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ተመድ በመግለጫው እንዳለው እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት በፈረንጆቹ 2000 መጀመሪያ ላይ ከዳርፉር ጦርነት ሸሽተው ነበር የተባሉ 16 ሽህ 200 የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የጄኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ልዑካን ቡድን በዳርፉር ግጭት ውስጥ በመንግስት እና በአማጺ ቡድኖች መካከል በፈረንጆቹ ጥቅምት 2020 የሰላም ስምምነት ፈራሚዎችን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት ተወካዮች፣ ፖሊስ፣ የመንግስት የደህንነት ሰዎችን ያካተተ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
ልዓላዊ ምክር ቤቱ በመግለጫው ተልዕኮው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዳጋሎ ወደ ምዕራብ ዳርፉር ካደረጉት ጉዞ ጋር ተመሳሳይ ነው ብሏል።
የኒያላ ግዛት መንግስት የሰሞኑ ግጭት በዘላኖች የተፈፀመ ጥቃት ነው ያለ ሲሆን፤ ይህም ሰፊ ጦርነት ቀስቅሷል ብሏል።
በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ከመከላከያ ሰራዊት የተውጣጡ ወታደሮች እና የዳጋሎ ፈጣን ድጋፍ ሰጭ ኃይሎችን ጨምሮ የጋራ ኃይል ወደ አካባቢው ተልኳል ነው የተባለው።