ሱናክ ከሰሞኑ በጉዞ ላይ በሚገኝ ተሽከርካሪ ውስጥ የደህንነት ቀበቶ ሳያደርጉ የቪዲዮ መልዕክት ቀርፀው ማስተላለፋቸው ይታወሳል
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በተሽከርካሪ ውስጥ የደህንነት ቀበቶ ሳያደርጉ በመጓዛቸው ተቀጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በላንክሻየር በጉዞ ላይ እያሉ መንግስታቸው የዜጎችን ህይወት ለማሻሻይ በያዛቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ የቪዲዮ መልዕክት ቀርፀው አስተላልፈዋል።
በወቅቱ ለደህንነታቸው ወሳኝ የሆነውን ቀበቶ አለማድረጋቸውን የተመለከቱ ብሪታንያውያንም ቪዲዮው ስር አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
"ጉዞ ላይ ባለ ተሽከርካሪ ውስጥ የደህንነት ቀበቶ ሳያደርጉ እንዴት ቪዲዮ ይቀርፃሉ" ያሉ የሀገሪቱ ፓለቲከኞችም ሱናክ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
የላንክሻየር ፖሊስም ሱናክ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ከተጠያቂነት አያስመልጣቸውም በሚል የ100 ፓውንድ የቅጣት ደብዳቤን ሰዶላቸዋል።
ለተፈጠረው ችግር ይቅርታን የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በ28 ቀናት ውስጥ ቅጣቱን መክፈል ይኖርባቸዋል።
ቅሬታ ካቀረቡም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ቅጣቱም እስከ 500 ፓውንድ ሊደርስ ይችላል ነው የተባለው።
የ42 አመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የኮሮና ክልከላን በመተላለፍ ከባለቤታቸው ጋር በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ልደት ላይ በመገኘትም ቅጣት እንደተላለፈባቸው ይታወሳል።
በብሪታንያ እድሜያቸው ከ14 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች በጉዞ ላይ የደህንነት ቀበቶዎችን ማድረግ እንደሚገባቸው በህግ ተደንግጓል።
ከ14 አመት በታች ያሉ ህፃናት የደህንነት ቀበቶ ባለማድረጋቸው ለሚመጣው አደጋም አሽከርካሪው ሃላፊነት ይወስዳል።
በሀገሪቱ በ2021 በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች ውስጥ 30 ከመቶው የደህንነት ቀበቶ ያላደረጉ እንደነበሩ ኢንዲያን ቱዴይ አስታውሷል።
ለንደን የደህንነት ቀበቶ ሳያደርጉ የሚነዱ አሽከርካሪዎች የሚተላለፍባቸው ቅጣት በሪከርድነት እየተመዘገበ መንጃ ፈቃድን እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ ለመውስድ አስባለች ነው የተባለው።