ስዊድን ለሩሲያ ሲሰልሉ ነበር ባለቻቸው ሁለት ዜጎቿ ላይ ክስ መሰረተች
የስዊድን አቃቤ ህግ እንዳለው ተከሳሾቹ ለሞስኮ ሲሰልሉ የነበሩት ከ2011 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው
ወንድማማቾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የእድሜ ልክ እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል ተብሏል
ስዊድን ለሩሲያ ወታደራዊ መረጃ አገልግሎት (ጂአርዩ) ሲሰልሉ ነበር ባለቻቸው ሁለት ስዊድናውያን ወንድማማቾች ላይ ክስ መመሰረቷን አቃቤ ህግ አስታወቀ።
የስዊድን አቃቤ ህግ እንዳለው ተከሳሾቹ ለሞስኮ ሲሰልሉ የነበሩት ከ2011 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።
ዋና አቃቤ ህግ ፐር ሊንድኲቪስት በሰጡት መግለጫ ፓያም ኪያ እና ፔይማን ኪያ የተባሉት ወንድማማቾች ወንጀሉን ስለመፈጸመቻው የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰው " የውጭ ኃይል እጅ ካለ በስዊድን ደህንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል" በማለት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱ ተናግረዋል።
የስዊድን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ሁለቱ ወንድማማቾች ፓያም ኪያ (35 አመት) እና ፔይማን ኪያ የስዊድን ዜግነት ቢኖራቸውም (42 አመት) የኢራን ተወላጆች ናቸው።
ፔይማን ኪያ በስዊድን የስለላ አገልግሎት /ሳፖ/ እና በስዊድን ጦር ውስጥ የስለላ ክፍል ውስጥ አገልግሏል።
በተጨማሪም በአንድ ወቅት በወታደራዊ ሚስጥራዊ አገልግሎት በጣም ሚስጥራዊ በሆነ ክፍል ውስጥ ለልዩ መረጃ ሰብሳቢ (ኬኤስአይ) ሆኖ የሰራ መሆኑ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመላክታሉ ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
እናም ከሳፖ እና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀጥሮ በነበረበት ወቅት በህገ ወጥ መንገድ መረጃ በማግኘቱ ተከሷል።
ወንድሙ ፓያም ኪያም እንዲሁ "በድርጊቱ እቅድ ውስጥ በመሳተፍና ከሩሲያ እና ጂአርአይ ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር መረጃን በማስተላለፍ እና ካሳ መቀበልን ጨምሮ" ተከሷል።
ወንድማማቾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የእድሜ ልክ እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል ተብሏል።
ይሁን እንጅ ፓያም ኪያ እና ፔይማን ኪያ ክሱን ውድቅ ማድረጋቸውን የስዊድን ሚዲያ ዘግቧል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ፓል ጆንሰን አርብ ዕለት ለሀገሪቱ ፓርላማ እንደተናገሩት ጉዳዩ “በጣም አደገኛ” ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ ከአንድ አመት ተጠርጣሪዎቹን ከአንድ አመት በፊት በቁጥጥር ስር ካዋለች በኋላ ደህንነቷን አጠናክራለች ሲሉም ተደምጠዋል ሚኒስትሩ።