ጳጳስ በስለት በመውጋት የተጠረጠረው ልጅ የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተበት
ልጁ በክሱ ጥፋተኛ ከተባለ እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል
ፖሊስ በአውስትራሊያ ሲድኒ ጳጳስን በቢለዋ በመውጋት የተጠረጠረውን የ16 አመት ልጅ የሽብር ክስ እንደመሰረተብ ገልጿል
የሲድኒውን ጳጳስ በስለት በመውጋት የተጠረጠረው ልጅ የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተበት።
ፖሊስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአውስትራሊያ ሲድኒ ጳጳስን በቢለዋ በመውጋት የተጠረጠረውን የ16 አመት ልጅ የሽብር ክስ እንደመሰረተበት ሮይተርስ ዘግቧል።
ታዋቂው የአሳይሪያ ኦርቶዶክ ቤተክርስቲያንን ጳጳስ ማር ማሪ ኢማኑኤል በስለት የመወጋት አደጋው የደረሰባቸው በምዕራብ ሲድኒ ዌክሊይ በሚገኘው የ'መልካም እረኛ ' ቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ በነበረት ወቅት ነው።
ከቦታው የተለቀቀው ቪዲዮ ልጁ በምዕመያን ሲገፈተር እና እስልምናን ሰድበዋል ባላቸው ኢማኑኤል ላይ ሲጮህ ታይቷል።
ፖሊስ እንደገለጸው አሁን ሆስፒታል ውስጥ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን ልጅ ጳጳሱን ለስድስት ጊዜ ያህል በመውጋት ጠርጥሮ ከሶታል። ልጁ በክሱ ጥፋተኛ ከተባለ እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል። ልጁ ያቀረበው የዋስትና መብት ተነፍጎታል።
ከዚህ ጥቃት በኋላ በርካቶች ወደ ቤተክርስሲያኗ በማምራት እና ልጁን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጥረት ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።
ከሰአታት በኋላ በአውስትራሊያ ከሚኙት ትላልቅ መስጂዶች ውስጥ አንዱ የሆነው ላከምባ መስጂድ የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደርሶበታል።
ይህን ተከትሎም በሂጃባቸው ብቻ የሚለዩት ሙስሊም ሴቶች ጥቃት ይደርስብናል ብለው ስጋታቸውን እየገለጹ መሆናቸው የላከምባ መስጂድን ጨምሮ ሶስት መስጂዶችን የሚቆጣጠረው የሊባኖስ ሙስሊም ማህበር ጸኃፊ ጋመል ኬይር ተናግሯል።
በቦንዲ ከተፈጸመው በጅምላ የስለት መውጋት አደጋ ከቀናት በኋላ የተከሰተው በኢማኑኤል ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለወትሮው ሰላም የነበረችውን ሲድኒን ጫፍ ላይ አድርሷታል ተብሏል። ከተማዋ የጠብመንጃ እና የቢለዋ መውጋት አደጋ ዝቅተኛ የሆነባት እና ከአለም ሰላማዊ የምትባል ነበረች።
ጳጳስ አማኑኤል በትናንትናው እለት ለሰላም እንደሚጸልዩ እና ለአጥቂያቸው ይቅርታ እንዳደረጉለት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ተናግረዋል።
ኪይር ላቀረቡት የሰላም መልእክት እና ይቅርታ ጳጳሱን አመስግኗል።