የአፍሪካ ህብረት በሱዳናውያን መካከል በሚደረገው ወይይት ላይ ላለመሳተፍ ወሰነ
የህብረቱ ተወካይ "የሱዳናውያን ቤታቸውን ለማስተካከል የመረጡትን ማንኛውንም ዘዴ ህብረቱ አይቃወምም" ብለዋል
ህብረቱ ውይይቱ “የግልጽነት፣ታማኝነት እና አሳታፊነት ችግር ያለበት” መሆኑን ገልጿል
የአፍሪካ ህብረት በሱዳናውያን መካከል በሚደረገው ወይይት ላለመሳተፍ መወሰኑን በካርቱም የአፍሪካ ህብረት ተወካይና የሶስትዮሽ የውይይት አመቻች ቃል አቀባይ አምባሳደር መሀመድ በላይሽ አስታወቁ።
ተወካዩ ይህን ያሉት በትናንትነው እለት የገንዘብ ሚኒስትሩ ዶ/ር ገብርኤል ኢብራሂም፣ የፍትህ እና የእኩልነት ንቅናቄ ፕሬዝዳንት፣ አምባሳደሮችን፣ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮን ሃላፊዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ነው።
ስብሰባው በሱዳን በአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ እና የተባበሩት መንግስታት የተቀናጀ የሽግግር እርዳታ ተልዕኮ የተዋቀረው የሶስትዮሽ ወገን በፖለቲካዊ ሁኔታ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ስለሚደረገው ውይይት የተመከረበት እንደነበረም ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ፤ በሱዳናውያን የሰላም ውይይት ሂደት ደስተኛ ያልሆነው የአፍሪካ ህብረት በሱዳናውያን መካከል በሚደረገው ወይይት ላለመሳተፍ መወሰኑን በተወካዩ አማካኝነት ግልጽ አድርጓል።
ህብረቱ በውይይቱ ላለመሳተፍ እንደምክንያት ያስቀመጣቸው ደግሞ ውይይቱ የግልጽነት፣ የታማኝነት እና የአሳታፊነት ችግር አለበት የሚሉ ናቸው።
በካርቱም የአፍሪካ ህብረት ተወካይና የሶስትዮሽ የውይይት አመቻች ቃል አቀባይ አምባሳደር መሀመድ በላይሽ፤ በትናንትነው እለት ከብሄራዊ ስምምነት ቡድን እና የነጻነትና የለውጥ ሃይሎች ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ግልጽነት፣ ታማኝነት እና አሳታፊነት በሌለበት ሁኔታ የአፍሪካ ህብረት መሳተፍ አይችልም" ብለዋል።
ህብረቱ ሁሉም ተዋናዮች በእኩል ደረጃ በማይታዩበት እና በማይከበሩበት ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ይቸገራል ሲሉም ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።
አምባሳደር በላይቼ "የአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት ሚና እንዲኖረው አይጠይቅም እንዲሁም የሱዳን ወንድሞች ቤታቸውን ለማስተካከል እና ቀውሳቸውን ለመፍታት የመረጡትን ማንኛውንም ዘዴ አይቃወምም" ብለዋል።
የዳርፉር ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ መሪ ሚናዊ በበኩላቸው፤ ለነፃነትና የለውጥ ኃይሎች እንዲሁም ብሔራዊ ስምምነት ቡድን በውይይት ተሳትፏቸው ያስተዋሉት ነገር ቢኖር አሁንም ዋና ዋና አብዮታዊ ኃይሎች በውይይቱ አለመሳተፋቸው እንደነበር ገልጿል።
የሱዳን ብሔራዊ ስምምነት ቡድን (ናሽናል አኮርድ ግሩፕ) በበኩሉ፤ በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት ሁሉም የሱዳን ወገኖች በማንኛውም የውይይት ሂደት ላይ እንዲገኙ ጠይቋል።