ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቅ ወሰነ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18 ነበር ከስራ ቦታ በጸጥታ ኃይሎች የተያዘው
ጋዜጠኛው ከሀገር እንዳይወጣ ለኢሚግሬሽን ትዕዛዝ እንደተሰጠ ፍርድ ቤቱ አሳውቋል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ተወሰነ።
ዋስትናውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው በአብላጫ ድምጽ የፈቀደው።
በዐቃቤ ሕግ ሦስት የወንጀል ክሶች የቀረቡበት የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም የ100 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቅዶለታል፡፡
በተመስገን የዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ የቀጠረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ የዋስትና ብይኑን በዳኞች የአብላጫ ድምጽ መስጠቱን ጠበቃው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ገልጸዋል፡፡
ሁለት ዳኞች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ተለቆ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ሲወስኑ አንዱ ዳኛ ግን በሀሳብ ተለይተዋል፡፡ ሁለቱ ዳኞች የ100 ሺህ ብር ዋስትናውን የፈቀዱት ከዚህ በፊት የተደረጉ ክርክሮችን በመዳደሰስ መሆኑን ነው አቶ ሄኖክ የገለጹት፡፡
ፖሊስ፤ በእነ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ይግባኝ ጠየቀ
ዳኞቹ በጋዜጠኛ ተመስገን ከቀረቡበት ክሶች መካከል “ሁለቱ ክሶች ቀላል መሆናቸውን” በመግለጽ፣ እንዲሁም “ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ሊሰራ ይችላል” በሚል የቀረበውን መቃወሚያ በተመለከተ ደግሞ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ሕገመንግስታዊ መብት በመሆኑ “ከወዲሁ ክልከላ ሊደረግ አይችልም” በማለት የዋስትና ብይኑን መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ቋሚ አድራሻ ያለውና የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ሊቀርብ የሚችል በመሆኑ፣ ቢለቀቅ ፍርድ ቤት ላይቀርብ ይችላል በሚል በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን መቃወሚያም ሁለቱ ዳኞች ባለመቀበል ከውሳኔው ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡
ሆኖም ክርክሩ በሚካሔድበት ጊዜ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ከሀገር እንዳይወጣ ለኢሚግሬሽን ትዕዛዝ እንደተሰጠ ፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቤተሰባቸው የተባለውን ዋስትና ለማስያዝ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ነው ጠበቃው የገለጹት፡፡
ነገር ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ጋዜጠኛው ገና ከእስር ነጻ አልወጣም፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የቀረቡበት ሦስት የወንጀል ክሶች “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ መግለፅ” ፣ ”የሐሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት” እና “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር መፈፀም” የሚሉ ናቸው፡፡
ዛሬ የተሰጠው የዋስትና መብት ተፈጻሚ ከሆነ፣ ከግንቦት 18/2014 ዓ.ምጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን የ100 ሺህ ብር ዋስ በማስያዝ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ የሚከታተል ይሆናል፡፡
aXA6IDE4LjIyNS4xMTcuMTgzIA==
ejasoft island