“በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለንም”- ተ.መ.ድ
በጄኔቭ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ከጽህፈት ቤቱ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ኃላፊ ጋር ተወያይተዋል
የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብም አስታውቋል
የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻች ከማበረታታት ባሻገር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብም አስታውቋል፡፡
በጄኔቭ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ የጽህፈት ቤቱ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ኃላፊ ለሆኑት ፍራንሷ ሚያንዳ መንግስት በትግራይ ክልል ስለወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሰፊ ገለፃ ሰጥተዋል እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ።
ሕወሀት ጁንታ ቡድን የተደራጁ ምዝበራ እና በወታደራዊ ኃይል የታገዝ መጠነ ሰፊ የሕግ ጥሰት ሲፈፅም መቆየቱንና የየአገሪቷን ሕልውና ጭምር አደጋ ላይ ለመጣል ሌት ተቀን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀውላቸዋል።
የህግ ማስከበር ዘመቻው በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ከባድ የአገር ክህደት ወንጀል የፈፀመውን የሕወሀት ቡድን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ ያሰማራቸውን የጥፋት ኃይሎች ትጥቅ በማስፈታት በክልሉ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ነው አምባሳደር ዘነበ ያብራሩት፡፡
ፍራንሷ ሚያንዳ በበኩላቸው ጽ/ቤቱ እንደ ሰብዓዊ መብቶች ተቋም የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ፣ ተፈናቃዮች ተገቢው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻች ከማበረታታት ባሻገር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ጽ/ቤቱ መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት የሚከታተልና የሚደግፍ መሆኑን ነው ሚያንዳ የገለጹት።