የግብጽ ፕሬዝዳንት፤ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም ዓለም አቀፍ ጥሪ አቀረቡ
ግብጽ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ኩፉኛ ከተጎዳ ሀገራት መካከል ናት
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ፤ መላው ዓለም በዚህ ጦርነት እየተሰቃየ ነው ብለዋል
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም ዓለም አቀፍ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጥሪውን ያቀረቡት በግብጽ ሻርም አል ሼክ ከተማ እየተካሄደ ባለውና በርካታ የዓለም መሪዎች በተገኙበት 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ-27) ላይ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር “እኔ የምናገረው እኛ ፤ በቀጠናው ምንገኝ ብቻ ስለምንሰቃይ ሳይሆን መላው ዓለም በዚህ ጦርነት እየተሰቃየ እንደሆነ አስባለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ከፈቀዱልኝ በስሜ እና በእናንተ ስም ይህን ጦርነት፣ ውድመትና ግድያ ለማስቆም በዚህ ጉባዔያችን ጥሪ አስተላልፋለሁ” ሲሉም
ዓለም አቀፋዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ።
አል ሲሲ በዩክሬን ምድር በመካሄድ ላይ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በሚደረግ ጥረት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውም ተናግረዋል፡፡
ስንዴን በመሸመት በዓለም አንደኛ እንደሆነች የሚነገርላት ግብጽ፤ የእህል ምርቶች ግዢ የምትፈጽምባቸው ዋናዎቹ ሀገራት በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን በመሆናቸው ጦርነቱ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደፈጠረ ይገለጻል፡፡
ጦረነቱ መጀመሩን ተከትሎ ተከትሎ ያጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት/አይ.ኤም.ኤፍ/ ድጋፍ እስከመማጸን አድርሷታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ጦርነት ዓለም አቀፍ መፍትሄ ካልተበጀለት በስተቀረ ቀድሞውንም የተናወጠውና በኮቪድ ወረርሺኝ የተመታው የዓለም ኢኮኖሚ፤ ውድቀት ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ባንክ በቅርቡ ማስጠንቀቁ አይዘነጋም፡
“የኢኮኖሚ ውድቀቱ” በተለይም በደምብ ባላደጉ የአውሮፓና ምስራቅ እስያ ሀገራት የከፋ እንደሆነም ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ለዓመታት የሚዘልቅ አቀፍ የምግብ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ጸሃፊው ጦርነቱ በተለይም በደሃ ሀገራ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን አዳጋች እያደረገው አንደሆነ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከዩክሬን በስፋት ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ የነበሩ እንደ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ እና በቆሎ ያሉ ምርቶችን ስርጭት እንዲቆም ማደረጉንም ጉቴሬዝ ተናግረዋል።
ይህም ዓለም አቀፍ የምግብ አቅርቦት እንዲቀንስ እና በዓለም ገበያ ያለው የምግብ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉንም አስታውቀዋል።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን ያሳያል።