የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር የነገው ምርጫ ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መንገድ እንዲዘገብ ጠየቀ
ችግር የሚገጥማቸው ባለሙያዎች ካሉ እንዲያሳውቁትም ማህበሩ ጠይቋል
ማህበሩ ለጋዜጠኞቹ ተገቢውን መረጃ መስጠት ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ግዴታ ነው ብሏል
ነገ የሚካሄደውን 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መንገድ እንዲዘገብ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA) አሳሰበ፡፡
ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ መልካም ምኞቱን የገለጸው ማህበሩ ሁኔታውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው የነገው ምርጫ ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መንገድ እንዲዘገብ ጠይቋል፡፡
የሚመለከታቸው አካላት ለጋዜጠኞቹ ተገቢውን መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸውም ነው ማህበሩ ያሳሰበው፡፡
ራሱን ማህበሩን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ሲሰጡ የነበሩት ሙያዊ ስልጠናዎች የምርጫ አዘጋገብንና መረጃ ማንጠርን ታሳቢ ማድረጋቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
በመሆኑም ምርጫውን ለመዘገብ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከወገንተኝነት የፀዱ፣ ሚዛናዊ፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያደርሱ አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል፡፡
ይህም በሀሰተኛና ቅይጥ መረጃዎች ስርጭት ምክንያት የሚያጋጥሙ ውዥንብሮችን ለማስቀረት የላቀ አበርክቶ ይኖረዋልም ነው ያለው ማህበሩ፡፡
ምርጫ ቦርድ የመረጃ ማጣራት ቡድን ከመመስረት ባሻገር ዕለታዊ መግለጫዎችን ለመስጠት መሞከሩንም አድንቋል፡፡
ችግር የሚገጥማቸው ባለሙያዎች ካሉ ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ለማህበሩ ጭምር እንዲያሳውቁ ጠይቋል።
በምርጫ ወቅት ከሚታዩ ሂደቶች የድምፅ አሰጣጥ ዋነኛው ነው ያለው ማህበሩ ከ38 ሚሊዮን በላይ ዜጎች (የጳጉሜ መራጮችን ጨምሮ) ለምርጫ ተመዝግበው የሚገኙበትን ምርጫ ለመዘገብ በርካታ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተዘጋጅተዋል ብሏል።
68 የሚዲያ ተቋማትና 1 ሺ 400 ዘጋቢዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘጋቢነት ፈቃድ መሰጠታቸውንም ነው የገለጸው።
89 ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፈቃድ ተሰጥቷቸው አገር ውስጥ ገብተው ወደተለያዩ የሃገሪቱ የምርጫ አካባቢዎች መሰማራታቸውንም የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን የትናንት መግለጫ ዋቢ አድርጎ አስቀምጧል፡፡