ደምቢያን ጨምሮ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
በደምቢያ 3 አስፈፃሚዎች መያዛቸውንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው
ቦርዱ ባጋጠሙ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የነገው ምርጫ በደምቢያ፣ በተሁለደሬ፣ በግንደበረት እና በነገሌ ምርጫ ክልሎች አይካሄድም ብሏል
የቁሳቁስ ስርጭትን በተመለከተት በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
የደንቢያ የምርጫ ክልል ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው መገኘታቸውን ያስታወቀው ቦርዱ በሳጥኖቹ መከፈት ምክንያት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ውስጡ ያለው ነገር መታየቱን ገልጿል።
የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችን መነካካት፣ መክፈት በጥብቅ የተከለከለ የወንጀል ተግባር በመሆኑ ይህን ያደረጉ ሶስት የደምቢያ አስፈፃሚዎች ተይዘው ምርመራ እንዲደረግ ለፌዴራል ፖሊስ ደብዳቤ መጻፉንም አስታውቋል።
ቦርዱ ዛሬ አመሻሹ ላይ (ከደቂቃዎች በፊት) ምርጫውን የተመለከተ ዕለታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው በተሁለደሬ 1 እና 2 ምርጫ ጣቢያዎች በተመሳሳይ መልኩ ሰማያዊ ሳጥን ተከፍቶ በድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ ያሉት እጩዎች እነማን እንደሆኑ የማየት ነገር ነበር ያለም ሲሆን ነገ በሁለቱም ምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ እንደማይሰጥ አስታውቋል።
ቦርዱ በኦሮሚያ ክልል በግንደበረት የምርጫ አስፈጻሚዎች እጥረት ማጋጠሙንም ገልጿል፡፡
ወረዳው አጋጣሚውን በመጠቀም ከቦርዱ እውቅና ውጭ አስፈጻሚዎችን በማሰልጠን ለማሰማራት ሲሞክር ተገኝቷል ያለም ሲሆን በዚሁ ምክንያት ነገ በግንደ በረት ድምጽ እንደማይሰጥ ይፋ አድርጓል፡፡
እጩ ይቀየርልን በሚል ከምርጫው አንድ ቀን በፊት በተወሠኑ ፓርቲዎች የቀረቡለትን ጥያቄዎች አለመቀበሉንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡