በህወሓት ቡድን አባላት ላይ የንብረት እግድ መጣሉን የፌዴራል የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ
ንብረታቸው ከታገደ ግለሰቦች መካከል የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሀይማኖት ይገኛሉ
የሸኔን ቡድን በገንዘብ ሲደግፉ ነበሩ የተባሉ 141 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳብም መታገዱ ተገልጿል
አዲስ አበባ የሚገኙ ቋሚ ንብረቶቻቸውን በቤተሰቦቻቸውና በወኪሎቻቸው አማካኝነት በማከራየትና ከፍተኛ ገቢ በመሰብሰብ ለሽብር ተልዕኮ እያዋሉ ባሉ ፣ በሽብር የተፈረጀው የህወሓት ቡድን አባላት ላይ የንብረት እግድ የተጣለ መሆኑን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት ከህወሓት ቡድን ጋር ተሰልፈው ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦች፤ ቀደም ሲል ለህዝብና ለሀገር ጥቅም እንዲሰሩ የተጣለባቸውን ከባድ ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው ከፍተኛ ሃብት በመመዝበር በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንብረቶች አፍርተዋል ብሏል ግብረሀይሉ በመግለጫው፡፡
በተጨማሪም በፈፀሙት የሀገር ክህደት ወንጀል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እንደነበርም አስታውሷል፡፡
መግለጫው አክሎም፤ እነዚህ ግለሰቦች በአንድ በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም፣ ግጭትና ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሰው የህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር በአመራርነትና በአባልነት እየተሳተፉ ይገኛሉ ነው ያለው።
ግለሰቦቹ ከህዝብና ከሀገር በመዘበሩት ሃብት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የገነቧቸውን የመኖሪያ ህንፃዎችና ያቋቋሟቸውን የንግድ ድርጅቶች በቤተሶቦቻቸውና በወኪሎቻቻው አማካኝነት በማከራየት በወር እስከ 9ሺህ ዶላር ድረስ ይሰበስቡ ነበር ተብሏል፡፡
ግለሰቦቹ ይህን ከኪራይ የሚገኝ ከፍተኛ ገቢ በህገወጥ መንገድ በመላክ የሽብር ቡድኑን ህልውና ለማስቀጠል ለተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ግዢ እንዲሁም ለሎጀስቲክስ አቅርቦት ከማዋል ባሻገር ንብረቶችን በመሸጥም ጭምር ሃብት የማሸሽ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ እያሉ በተደረገባቸው ጥብቅ የመረጃ ስራና ክትትል ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማቅረብ እግዱ በፍርድ ቤት በኩል እንዲፈጸም መደረጉን መግለጫው አመልክቷል፡፡
ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱና እንዲታገድ የተደረገባቸው የህወሓት ቡድን አመራርና አባላት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በቅፅል ስሙ ወዲ ወረደ፣ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ በቅፅል ስሙ ፍስሃ ማንጁስ ፣ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሀይማኖት በቅፅል ስሙ ጆቤ፣ሜጀር ጀነራል ሀልፎም እጅጉ በቅፅል ስሙ ወዲ እጅጉ፣ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ ግደይ፣ብርጋዴር ጀነራል ሃ/ስላሴ ግርማይ በቅፅል ስሙ ወዲ እንቤተይ፣ብርጋዴር ጀነራል ምግበ ሀይለ፣ ብርጋዴር ጀነራል ተክላይ አሸብር በቅፅል ስሙ ወዲ አሸብር፣ አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ፤አቶ ሀሰን ሽፋ በድምሩ አስራ ዘጠኝ (19) መሆናቸውን የጋራ ግብረኃይሉ ገልጿል።
መግለጫው አክሎም መቀሌ ከተማ ሆነው ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲሰጡ፤ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን በድብቅ ሲያቀርቡ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብሶችን በመልበስ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ተመሳስለው ጥቃት ሲፈጽሙ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል 14 የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ፤ለሰብአዊ ድጋፍ በመጓጓዝ ላይ የነበሩና እያንዳንዳቸው 20 ሌትር የምግብ ዘይት የያዙ 2ሺህ 200 ጄሪካኖችን የጫነ አንድ ተሽከርካሪ ከእነ ተሳቢው አስገድደው አቅጣጫውን እንዲቀይር በማድረግ፤ በድብቅ ለሽብር ቡድኑ ለመላክ ሲሞክሩ መሆኑን አትቷል፡፡
በተመሳሳይ በሽብር ወንጀል የተፈረጀውን የሸኔ ቡድን በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና ገንዘባቸው እንዲታገደ መደረጉንም ግብረ ኃይሉ አመልክቷል፡፡
በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች፣ በጅማና በዙሪያው በሚገኙ ወረዳዎች 27 አባላቱም በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ያመለከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤ ለቡድኑ ሊላኩ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶችም በተደረጉ ጥብቅ ክትትሎች በተለያዩ አካባቢዎች መያዛቸውን ገልጿል።
ሸኔ ባዋቀራቸው ሴሎች ዙሪያ ይደረግ በነበረው ክትትል ለቡድኑ ተገዝተው ሊላኩ የነበሩ 5ሺህ 661 የክላሽንኮቭ ጥይቶች፤ 2ሺህ የብሬን መትረየስ ጥይቶች፤ ሌሎች ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያ የሚውሉ ቁሶችና ሰነዶች እንዲሁም አዘዋዋሪዎቹም ጭምር ቡራዩ፣ጊንጪና ከአምቦ ወጣ ብላ በምትገኘው ባቢች በተባለች ቦታ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ሃይሉ መግለጫ ጠቁሟል፡፡
የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ “ለሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ” ቡድን አባላት የሽብር ተግባር የሚውሉ ህገወጥ ገንዘቦችን ምንጭ በተመለከተ ባደረገው ሚስጥራዊ ክትትል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት እንዲሁም በቶጎውጫሌ እና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር በህገወጥ መንገድ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በቁጥጥር ስር ማዋሉውንም በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም አንድ ሚሊዮን 267 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ከ900 ሺህ በላይ ዩሮ፣ እንዲሁም 90 ሺህ ፓውንድና ከ2 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር ከ 12 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተቀሰቀሰውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠርም መነሻውን ጋምቤላ መዳረሻውን አማራ ክልል በማድረግ በኮድ ሶስት የታርጋ ቁጥር አ/አ A25773 አይሱዝ የጭነት መኪና የታሸጉ ውሃዎችንና ሸቀጦችን እንደሽፋን በመጠቀም ሚስጥራዊ ቦታ ሻግ በማዘጋጀት 62 ክላሽንኮቭ ከ36 ካዝናዎች ጋር በድብቅ ለማሳለፍ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ህወሐትን እና ሸኔን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።