ፕሬዝዳንቷ “ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል” ብለዋል
“የሰማሁት ዜና ልቤን ሰብሮታል…” ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ
ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ፕረዝዳንት ሳህለ ወርቅ ድርጊቱን በማውገዝ የተሰማቸውን ሀዘን የገለጹበት መግለጫ የሚከተለው ነው፡
የሰማሁት ዜና ልቤን ሰብሮታል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የዛሬ አመት የተናገርኩት ከመድገም ዉጪ ሌላ ቃላት የለኝም፡፡
ዘርና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፣ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል: ለቅሶ፣ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው፡፡
ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል፡ አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን ፤ የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ፤ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል፡፡