መንግስት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠየቀ
በንጹኃን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በመዋቅራዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ጉባዔው ገልጿል
የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ የሕገ መንግስት ማሻሻያ መደረግ አለበት ብሏል
መንግስት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠየቀ
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መንግስት ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ጠይቋል፡፡
ጉባዔው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ከሁለት ቀናት በፊት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ ለተፈፀመው ጥቃት መንግስት መሰረታዊ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ማንነትን መሰረት በማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥቃቶች መዋቅሩ የሚፈጥራቸው በደሎች እንደሆኑም ነው መማክርት ጉባዔው ያነሳው፡፡ መማክርት ጉባዔው ጥቃቶቹ በመዋቅር ሚፈጸሙ በመሆናቸው የዚህ መነሻ የሆነው ሕገ መንግስት ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
የመማክርቱ ጉባኤ በመግለጫው በተለያዩ አካባቢዎች አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መንግስት ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግም አሳስቧል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ በአማራ ላይ የደረሱ የተለያዩ ጥቃቶች ችግሩን መዋቅራዊ በሆነ መልኩ መፍታት እንደሚያስፈልግ አመላካች በመሆናቸው ፣ አጽንኦት በመስጠት የፌዴራል መንግስቱ የማያዳግም አርምጃ እንዲወስድም ነው መማክርት ጉባዔው የጠየቀው፡፡
በተለያዩ ጊዚያት የተፈጸሙ ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ማንም ያቀናብራቸው ማን እንዳይፈፀሙ መከላከል እንዲሁም አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ እና ተጎጂዎችን የመካስ ኃላፊነት ክልሉን የሚያስተዳድረው መንግስት፣ የፌዴራል መንግስት እንዲሁም የገዥው የብልፅግና ፓርቲ እንደሆነም አስታውቋል፡፡
ችግሩ ከሕገ መንግስቱ የሚመነጭ እንደሆነ ያነሳው መማክርት ጉባዔው ፣ ስርዓታዊና መዋቅራዊ የሆነውን ጥቃት ማስቆም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡