የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በጽኑ እንደሚያሳስበው ዩኔስኮ አስታወቀ
“ሃይማኖታዊ የመዳረሻ፤ የሰላምና ፍቅር መገኛ ቅዱስ ስፍራ የሆነው ላሊበላ የግጭት መቀ ስቀሻ ሊሆን አይገባም”ም ነው ዩኔስኮ ያለው
ዩኔስኮ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናቱ እንዲጠበቁ ጥሪ አቅርቧል
የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በጽኑ እንደሚያሳስበው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አስታወቀ፡፡
ግጭቱ የዓለም ቅርስ የሆኑት ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ወደሚገኙበት የላሊበላ ከተማ መስፋፋቱ እጅግ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
ዩኔስኮ እጅግ የላቁ የዓለም እሴትና ቅርሶች ናቸው ያላቸው ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በዓለም አቀፍ ህግጋት መሰረት ቅርሶቹን ለጉዳት ከሚያጋልጡ ማንኛውም ድርጊቶች በመቆጠብ እንዲጠበቁ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግ የአካባቢውን ባህላዊ ሃብቶች ከዘረፋና ውድመት መጠበቅ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
“ሃይማኖታዊ የመዳረሻ፤ የሰላምና ፍቅር መገኛ ቅዱስ ስፍራ የሆነው ላሊበላ የግጭት መቀ ስቀሻ ሊሆን አይገባም”ም ነው ዩኔስኮ ያለው፡፡
ቤተ ጊዮርጊስ (ባለ መስቀል ቅርፁ) እና ቤተ መድሃኔ ዓለምን መሰል 11 ውቅር ዐብያተ ክርስትያናትን ያካተቱት የላሊበላ ቤተ እምነቶች እየሩሳሌምን ታሳቢ አድርገው በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላሊበላ የስልጣን ጊዜ የተገነቡ ናቸው፡፡
ውቅር ዐብያተ ክርስትያናቱ በ1979 ዓ.ም የአለም ቅርስ ሆነው በዩኔስኮ መመዝገባቸው የሚታወስ ነው፡፡
በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ከሰሞኑ ላሊበላን ተቆጣጥሯል መባሉ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ብዙዎች “ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ለጥቃት ይዳረጉ ይሆን?” በሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡