ሀጂ ዑመር እድሪስ "ከስልጣን እንደተነሱ ተደርጎ የተወሰነው ውሳኔ በየትኛውም ተቋም ተፈጻሚነት የለውም" ተባለ
ከእውቅና ውጭ ነው በተባለው በትናንቱ ስብሰባ አዲስ የመጅሊስ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ተመርጦ ነበር
ትናንት በሸራተን የነበረው ስብሰባ ከእውቅና ውጭ መሆኑ ተገልጿል
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ፤ ትናንት በሸራተን ሆቴል በተደረገ ስብሰባ ከሥልጣን መነሳታቸው በየትኛውም ተቋም ተፈፃሚነት እንደሌለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ም/ቤቱ በዛሬ መግለጫው፤ ትናንትና ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ``የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ውሳኔዎች`` በሚል በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል የተካሄደውን ስብሰባም ህገወጥ መሆኑን ገልጿል ፡፡
ህገ ወጥ የተባለው የሸራተኑ ስብሰባ ባካሄደው ምርጫ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሒም ቱፋ የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ አብዱልከሪም ሼኽ በድረዲን የመጅሊሱ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጦ ነበር።
ከዚህ ባለፈም በስብሰባው ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ እና ምክትላቸው ጄይላን ከድር (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የመጅሊሱ አመራሮችም ከቦታቸው እንዲነሱና የፈትዋ ምክር ቤት አመራር እንዲሆኑ ተወስኖ ነበር።
ውሳኔው ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ዛሬ አርብ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ/ም መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስብሰባውንም ሆነ የስብሰባውን ውሳኔ ውድቅ አድርጓል፡፡
``የሸራተኑ ስምምነት የተደረገው ከምንጩ እየደረቀ የነበረውን የሰለፊ- ወሃቢይ አስተሳሰብ ወደ ተቋሙ በማስገባት ከነባራዊ ሁኔታው በመረዳት ወደ ነባሩ እስልምና የሚቀየርበትን መደላድል ለመፍጠር`` የተደረገ ነውም ብሏል ጠቅላይ ምክር ቤቱ፡፡
መግለጫውን የሰጡት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ "የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባዔ" በሚል የተካሄደው ስብሰባ ሕገወጥ እንደሆነ ጠቅሰው``እርስ በእርስ የተሿሿመው ህገ ወጥ አካል ነው`` ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ በመግለጫቸው የሸራተኑ ስብሰባ በየትኛውም ተቋም ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፤ ስብሰባውን ያደረገው ቡድን ሚያዝያ 23 ቀን 2011 ዓ.ም ከሸራተን አዲስ ስምምነት ``ራሱን ነጥሎ ያደራጀ`` እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በአዋጅ ህጋዊ ዕውቅና የተሰጠው ጠቅላይ ም/ቤቱ ከ14 ክ/ዘመናት በላይ ባስቆጠረና የነባሩ እስልምና ተከታይ በሆኑ የሃይማኖት አባቶች የተቋቋመ ነባር ተቋም በመሆኑ ``የመሻይኾቻችን መንገድ የሆነውን የአህሉ ሱና ወልጀማዐ መስመር ያስቀጥላል`` ብለዋል ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ።
ጠቅላይ ም/ቤቱ በተጓደሉ የስራ አስፈጻሚ አባላት ምትክ ከዑለማዎች መካከል በመምረጥ ይተካል ያሉም ሲሆን፤ ከሀጁ ስራ ጎን ለጎን በሀገር አቀፍ ደረጃ የዲኑ ባለቤት የሆኑ ዑለማዎችን በመጥራትና ረቂቅ ሰነዶችን በማስጸደቅ ጠቅላይ ም/ቤቱን እንደሚያዋቅር ጠቅሰዋል፡፡