አረብ ኢሚሬትስ ለቻይና ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ድጋፏን ገለጸች
የአረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ“አንድ ቻይና” ፖሊሲን ማክበር እንደሚገባ አሳስቧል
ዩ.ኤ.ኢ አለማቀፍ ሰላምና መረጋጋት ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ግጭት ቀስቃሽ ጉብኝቶች እንደሚያሰጋት ገልጻለች
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ለቻይና ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ድጋፏን ገለጸች።
የአሜሪካ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን በመተው በታይዋን ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት ለቻይና ያላቸውን ድጋፍ በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
የአረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፤ የ“አንድ ቻይና” ፖሊሲን ማክበር እንደሚገባ አሳስቧል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው፤ የአረብ ኢሚሬትስ አለማቀፍ ሰላምና መረጋጋት ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ግጭት ቀስቃሽ ጉብኝቶች እንደሚያሰጋት ገልጿል።
ዓለም አቀፍ ሰላ እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ለዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም አሳስባለች።
የአሜሪካ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲን የቻይናን ዛቻ ወደ ጎን በመተው ወደ ታይዋን መጓዛቸውን ተከትሎ በቻይና-ታይዋን ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ይታወቃል።
ቻይና አሜሪካ በዴሞክራሲ ሽፋን ሉአላዊነቴን ተዳፍራለች ያለች ሲሆን፤ ቻይናን የሚዳፈሩ ሁሉ ይቀጣሉ ማለቷ አይዘነጋም።
ሩሲያ፣ ሰሜን ከሮያ እና ኤርትራ ቻይናን በመደገፍ አቋማቸውን ያንፀባረቁ ሲሆን፤ ኤርትራ የፔሎሲን ጉብኝት ህግን የጣሰ ነው ስትልም ተችታለች።
ኢትዮጵያም ለረጅም ዓመታት ስታራምድ የቆየችውን የ"አንድ ቻይና” ፖሊሲ አቋሟን እንዳጸናች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።