መንግስት ኤምባሲዎች አዲስ አበባ እንደ ተከበበች በማስመሰል ከሚነዙት ሀሰተኛ መረጃ ኢንዲቆጠቡ አሳሰበ
“የመንግስት ባለስልጣናት ቪዛ እየጠየቁ ነው” የሚል የውሸት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላት መኖራቸውንም አስታውቋል
ሀገርን ማፍረስ ላይ የተጠመዱ ወገኖች ከድርጊታው ካልተቆጠቡ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል
የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙዪኒክሽን አገልግሌት በዛሬው እለት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም “ከህወሓት ጋር በሽርክና የሚሰሩ ሚዲያዎች የመጨረሻ ያሉትን የሽብር ወሬ በማሰራጨት ተጠምደዋል” ብሏል።
የእነዚህ አካላት ቁልፍ ኢላማቸው አድርገው የወሰዱት ደግሞ በአመራሩ፣ በህዝቡና በወገን ጦር መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር፣ ፍርሃት እንዲነግስ የማሸበር ስራ መሆኑንም አስታውቋል።
ፌስቡክ በትናትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባሳለፍነው ቅዳሜ በገጻቸው የለጠፉትን መልእክት ግጭት ያነሳሳል በሚል ከገፁ የሰረዘ ሲሆን፤ በመግስት በመግለጫው “ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲባባስ አብክረው የሚሰሩ እንደ ፌስቡክ አይነት የማህበራዊ ሚዲያዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መዕልክቶች ከገፁ በመሰረዝ አጋርነቱን አሳይቷል” ብሏል።
“እንደ ሮይተርስ ያሉት ደግሞ ያልተያዙ አካባቢዎችን እንደተያዙ በማስመሰል የተሳሳተ መረጃ እየዘገቡ ይገኛሉ” ሲልም አስታውቋል።
“በተለያየ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ተላላኪዎቻቸው የፀጥታ ችግር እንዳለ በማስመሰል የግል ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የማግባባት ስራ እየሰሩ ይገኛሉ” ብሏል መግለጫው።
“በህዝቡና በወገኑ ጦር ውስጥ ጥርጣሪዎችን ለመፍጠር የመንግስት ባለስልጣናት ቪዛ እየጠየቁ ነው በሚል የውሸት ፕሮፖጋንዳ እየነዙ ነው”ም ብሏል መግለጫው።
“ከዲፕሎማሲ መርህ ውጪ የአንዳንድ ሃገር ኤምባሲዎች አዲስ አበባ እንደ ተከበበች በማስመሰልና ያሰቡት ውጥን እንዲሳካ በኤምባሲያቸው የሚሰሩ ዜጎቻቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እያሳሰቡ ይገኛሉ” ያለው መግለጫው፤ በእንዲህ አይነት መንገድ ሀገርን ለማፍረስ የተጠመዱ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
“በሀገር ጉዳይ ቀልድ የለም” ያለው መንግስት ከድርጊቱ ባልተቆጠቡት ላይ “የማያዳግም ርምጃ” እንደሚወስድ አስጠንቋል።
“መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ኢትዮጵያን የማዳን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የምንገኝ መሆኑን ተገንዝቦ የጀመረውን ሀገር የማዳን ንቅናቄ አጠናክሮ እንዲቀጥል” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።