አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምትሰጥ ገለጸች
ዩክሬን ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ከአሜሪካ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አግኝታለች
አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ እንደምትቀጥልም አስታውቃለች
አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምትሰጥ ገለጸች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደለየለት ጦርነት ከገባች ዘጠኝ ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶታል።
ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ጥቃት ለመመከት ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት በተጨማሪ ከሌሎች ሀገራትም የገንዘብ እና የአይነት ድጋፎችን እያገኘች ነው።
አሜሪካ ጦርነቱ ከተጀመረበት ካሳለፍነው የካቲት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ረድታለች ተብሏል።
አሁን ደግሞ የ400 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ወደ ዩክሬን እንደምትልክ ቪኦኤ የፔንታጎን ቃል አቀባይን ጠቅሶ ዘግቧል።
እነዚህ የጦር መሳሪያዎች በአዲስ መልክ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ነው ለምትባለው ሩሲያ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደሆነም ተጠቅሷል።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን የጦር መሳሪያ፣ ገንዘብ እና የደህንነት መረጃዎች ድጋፏን እንደምትቀጥልበትም ዩክሬንን እየጎበኙ ያሉት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የጸጥታ አማካሪ ሱልቪያን ተናግረዋል።
ዋሸንግተን ከሌሎች 40 የአውሮፓ እና የአለማችን ሀገራት ጋር በመሆን ዩክሬን የሩሲያን ድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት መመከት የሚያስችሉ የጦር መሳሪያ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ከአሜሪካ ለተደረገላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ዋሸንግተን እና ሎሎችም ሀገራት ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
አሜሪካ የምክር ቤት አባላት ምርጫን ከቀናት በኋላ የምታካሂድ ሲሆን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደኑ ዲሞክራት ፓርቲ ድል ላይቀናው እንደሚችል ተሰግቷል።
ዲሞክራት ፓርቲ በሪፐብሊካኖች አብላጫ የኮንግረስ መቀመጫዎችን ካጡ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን የሚያደርጉት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሊቀንስ አልያም ሊቆም እንደሚችል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።