አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ725 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንደምትልክ አስታወቀች
ወታደራዊ እርዳታው ፑቲን በዩክሬን ከተሞች ላይ እየወሰዱት ያለውን የበቀል እርምጃ ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል
ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ ለዩክሬን የ18 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች
አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ 725 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንደምትልክ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ፔንታጎን አስታወቁ።
እርዳታው የመጣው "በሩሲያ በዩክሬን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባደረሰችው አሰቃቂ የሚሳኤል ጥቃት ምክንያት" እና "በሩሲያ ኃይሎች የሚፈጽሙትን የጭካኔ ድርጊት የሚያሳይ ማስረጃ ተከትሎ ነው" ሲሉ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
እርዳታው ለHIMARS ሮኬት ሲስተም የሚሆኑ ተጨማሪ ጥይቶች፣ ጸረ-ታንክ የጦር መሳሪያዎች፣ HARMs በመባል የሚታወቁ ጸረ-ጨረር ሚሳኤሎች፣ ተሸከርካሪዎች እና የህክምና አቅርቦቶች እንደሚያካትት የገለጸው ደግሞ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችው አጠቃላይወታደራዊ እርዳታ ወደ 18 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን አስታውቀዋል፡፡
"ዩክሬናውያን ነጻነታቸውን በሚያስገርም ጀግንነት እና ወሰን በሌለው ቁርጠኝነት እስኪያረጋግጡ ድረስ ከጎናቸው መሆናችንን እንቀጥላለን" ብለዋል ብሊንከን፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፤አሜሪካ 3 ቢልዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን እንደምትሰጥ ከአንድ ወር በፊት ነሓሴ 24 በዩክሬናውያን የነጻነት ቀን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የጆ ባይደን ንግግር ዩክሬናውያን ከሩሲያ ጋር እያደረጉት ባለው ጦርነት አሜሪካ የዩክሬን ትግልን ለመርዳት ያላትን ቁርጠኝነት እየቀጠለ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆነም ነበር ኤኤፍፒ በወቅቱ የዘገበው፡፡
የተሰጠው ድጋፍ ዩክሬን ፤በአየር መከላከያ እንዲሁም የመድፍ ስርዓቶችና ጥይቶችን እንድታጎለብት ብሎም ከረዠም ርቀት ጥቃቶች እራሷን መከላከል እንደምትችል ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ አመላክቷል፡፡
ድጋፉ አሜሪካ በተናጠል በጦርነትው ውስጥ ላለችው ለዩክሬን ካደረገችው ድጋፍ ትልቁ ነው የተባለለትም ነበር፡፡
በኮንግረስ ይሁንታ ባገኘውና በሀገራቱ መካከል በሚደረገው የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር መሰረት አሜሪካ እያደረገች ያለችው ወታደራዊ እርዳታ የአሜሪካ ኮንግረስ በግንቦት ወር ያጸደቀው የ40 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አካል እንደሆነም ነው የሚገለጸው፡፡
ጆ ባይደን አሜሪካ ለውጊያ ወደ ዩክሬን የምትልከው ወታደር እንደማይኖር ነገር ግን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡