አሜሪካ መንግስት አሁንም የአየር ላይ ጥቃቶችን እንዲያቆም ጥሪ አቅርባለች
የሃገር መከላከያ ሰራዊት ለጊዜው ወደ ትግራይ ክልል አይገባም መባሉን እንደምትቀበል አሜሪካ አስታወቀች፡፡
ዋሽንግተን ጦሩ ነጻ ባወጣቸው የአፋር እና የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ ታዟል መባሉን ተከትሎ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በኩል መግለጫ አውጥታለች፡፡
በመግለጫው ውሳኔውን እቀበላለሁ ያለች ሲሆን መንግስት አሁንም የአየር ላይ ጥቃቶችን እንዲያቆም እና ኤርትራም ኃይሎቿን እንድታስወጣ ጠይቃለች፡፡
ሁሉም የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን ማቆም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲያበቁ ማድረግ፣ ሰብዓዊ አቅርቦቶችን መፍቀድ እና መደራደር አለባቸው ያለችም ሲሆን ግጭቱ ምንም ዐይነት ወታደራዊ መፍትሔዎች እንደሌሉት ገልጻለች፡፡
የአሜሪካ መንግስት ቀደም ሲል የህወሓት ኃይሎች “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች መውጣታቸው ግጭቱን ለማስቆም እንደሚረዳ ገልጾ ነበር፡፡
ህወሓት “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ቢገልጽም የኢትዮጵያ መንግስት ግን የህወሓት ሀይሎችን በማሸነፍ ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች እንዲወጡ ማድረጉን ገልጿል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው መግለጫ የመንግስት ጦር የአፋር ክልልን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ምስራቅ አማራን ነጻ ማውጣቱንና ጦሩ ባለበት ጸንቶ እንዲቆይ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች በድጋሚ እንዳይከሰቱ በማሰብ ጦሩ ወደ ትግራይ በጊዜያዊነት እንዳይገባ መታዘዙም ተገልጿል፡፡
ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነቱ በሺዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡