በላሊበላና ሙጃ በኩል ጋሸናን ለመቁረጥ ሞክሮ የነበረው ወራሪ ኃይል ተደምሷልም ተብሏል
ወልዲያን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣታቸውን መንግስት አስታወቀ፡፡
ዛሬ ቆቦ፣ ሮቢት፣ ሳንቃ፣ሲሪንቃ፣ጎብዬና ሀራ ከተሞች የሚገኙበት የሰሜን ወሎ ዞን ሙሉ ለሙሉ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከህወሓት ወራሪ ቡድን ነጻ መውጣታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ አቶ ለገሰ ቱሉ ከደቂቃዎች በፊት አስታውቃዋል፡፡
ጦሩ ትናንት በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉ ሰንሰለታማ ተራሮችን ነጻ እንዳወጣ ተነግሮ ነበር፡፡
በአካባቢው የነበረው የህወሓት ጦር መደምሰሱን የተናገሩት ሚኒስትሩ ወደ ጨርጨርና አላማጣ እየፈረጠጠ ነው ብለዋል፡፡
አካባቢዎቹ አያሌ በደሎች ሲፈጸሙባቸው የነበሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በላሊበላና ሙጃ መካከል በመግባት ጋሸናን ቆርጦ ለመያዘው ሞክሮ የነበረው ኃይል ከበባ ውስጥ ገብቶ እንዲደመሰስ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
ጦሩ ወደ ሰቆጣና አካባቢው እየገሰገሰ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡