“ከአሁን ቀደም ካጋጠሙ ችግሮች መማር በማስፈለጉ ሰራዊቱ ባለበት ጸንቶ እንዲቆይ ታዟል”- መንግስት
መንግስት አስፈላጊ ያላቸውን እርምጃዎች በጥናት ላይ ተመርኩዞ በቀጣይነት እንደሚወስድም ነው የተገለጸው
ሰራዊቱ ነጻ አውጥቶ በያዛቸው የአፋር እና የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ጸንቶ ይቆያልም ተብሏል
በዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት የመጀመሪያ ግቡን አሳክቶ ተልዕኮውን አጠናቋል የተባለለት መከላከያ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ነጻ አውጥቶ በያዛቸው አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ መታዘዙ ተነገረ፡፡
ሰራዊቱ ሙሉ በሙሉ ነጻ ባወጣቸው የአፋር ክልል እና የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ መታዘዙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከሰዓት በፊት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አሁናዊ ግምገማዎች “የጠላት መሻት፣ ፍላጎት እና የማድረግ ዐቅም መመታቱን ያሳያሉ” ያሉት ሚኒስትሩ መንግስት “የጠላት ኃይል ፍላጎት ዳግም እንዳይቀሰቀስ” አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን እርምጃዎች በጥናት ላይ ተመርኩዞ በቀጣይነት እንደሚወስድ ገልጸዋል፤ አሁን ያለውን የአሸናፊነት ቁመና ለመጠበቅና በጥንካሬ ለመዝለቅ ጠንካራ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ በመጠቆም፡፡
ወልዲያን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጡ
ትዕዛዙ ከአሁን ቀደም በክልሉ ካጋጠሙ ችግሮች መማር በማስፈለጉ መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ ለውሳኔው መነሻ የሆኑ ሶስት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል፡፡
አቶ ለገሰ በክልሉ ይገኝ የነበረው ጦር እና ትጥቅ እንዳይወጣ ሲማጸን የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ሰሜን እዝ “አጸያፊ በሆነ መንገድ በክህደት ሲጠቃ” መከላከል ቀርቶ ድርጊቱን አለማውገዙን በመጀመሪያ ምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ጦሩ ክህደቱን በመቀልበስ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብና ህግ ለማስከበር ሲንቀሳቀስ ከኋላ ኋላ መመታቱንም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ችግሮቹ ዳግም እንዳያጋጥሙ እና ሰራዊቱን ተጠብቆ በተጠና መንገድ እርምጃዎችን እንዲወስድ በማሰብ ትዕዛዙ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በሽብር ቡድኑ ሴራና ወጥመድ ላለመግባት በማሰብ ውሳኔው መሰጠቱንም ተናግረዋል ሚኒስትሩ፡፡
በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የረገፉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹን የቻለውን ያህል ወስዶ በጅምላ ቀብሯል ያሉም ሲሆን ‘በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል’ በማለት መንግስት ላይ ለማላከክ እና ራሱን ከተጠያቂነት ለማሸሽ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል ብለዋል፡፡
ይህን በማስተጋባት ኢትዮጵያ ላይ ቀጣይነትና ፍርደ ገምድልነት ያለው ጫናን ለማሳረፍ የተዘጋጁ አንዳንድ ዓለም አቀፍ አካላት እንዳሉ እንደሚታወቅ በማስታወስም “መንግስታችንና ሰራዊታችንን ከእንደዚህ ዐይነት እኩይ ሴራ እና ወጥመድ መከላከል ስለሚገባ” ትዕዛዙ መሰጠቱንም ነው የገለጹት፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ሰራዊቱ የሃገርን ግዛታዊ አንድነትና ሰላምን ለአደጋ የሚዳርግ ሁኔታ ተፈጥሯል ተብሎ በሚታሰብበት በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በመግባት በትግራይ ክልል አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ህገ መንግስታዊ መብትና ግዴታ ያለው በመሆኑ ተላልፏልም ብለዋል፡፡
በሌሎቹ ግንባሮች በተለይም በምዕራብ አማራ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ውጤቶችና የመንግስት ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ወደፊት የምናሳውቅ ይሆናልም ነው አቶ ለገሰ ያሉት፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሸኔ ታጣቂዎች የሚደርሱ ጥፋቶችን ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡