አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ11 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍ ልታደርግ መሆኑን አስታወቀች
የጦር መሳሪያ ድጋፉን የሀገሪቱ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ጥያቄ ቀርቧል
አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን የለገሰችው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል
አሜሪካ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታወቀች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ 193ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ዩክሬንን በመደገፍ የጦር መሳያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ሲሆኑ ዋሸንግተን ብቻዋን ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ድጋፍ አድርጋለች።
ከቀናት በፊት ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን የሰጠችው አሜሪካ አሁን ደግሞ ተጨማሪ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ እሰጣለሁ ብላለች።
የፕሬዝዳንቱ ጸህፈት ቤት አዲሱን ጦር መሳሪያ ድጋፍ የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ጥያቄ ማቅረቡን በድረገጹ አስነብቧል።
ጽህፈት ቤቱ በአጠቃላይ 47 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ኮንግረሱ በአስቸኳይ ድጋፍ ፕሮግራም እንዲያጸድቅለት የጠየቀ ሲሆን ለዩክሬን ከሚለገሰው 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ወጪ ያለው በጀት ለዝንጆሮ ፈንጣጣ እና ለኮሮና ቫይረስ ስራዎች ማቀላጠፊያ ይውላል ተብሏል።
አሜሪካ አሁን ከምትሰጠው የ11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ውስጥ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላሩ በቀጥታ ለወታደራዊ ድጋፍ የሚውል ሲሆን ቀሪው ለወታደራዊ ደህንነት ስራዎች ይውላል ተብሏል።
ሩሲያ ምዕራባውያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ማስታጠቃቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ባለፉት ጊዜያት ውስጥም አሜሪካንን ጨምሮ ከምዕራባዊያን ለዩክሬን የተለገሱ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን አውድሜያለሁ ማለቷም አይዘነጋም።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በየዕለቱ እስከ 200 ወታደሮች በሩሲያ ጥቃት እየተገደሉባቸው እንደሆነ ገልጸው ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እንዲለግሱም ጥሪ አስተላልፈው ነበር።