ወጣቱ ሃብታም ነው ካለው አጎቱ ብር ለመቀበል በማሰብ ድርጊቱን መፈጸሙን ገልጿል
“ታግቻለሁ” በሚል ቤተሰቦቹ 350 ሺ ብር እንዲከፍሉ የጠየቀው የወረታ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ስጦታው አዘዘ በሕግ መያዙን የወረታ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
ብሩን የጠየቀው ወጣት ስጦታው፤ ጓደኛው መታገቱን ለቤተሰቦቹ በስልክ እንዲነግርለትና ቤተሰቦቹም ለማስለቀቂያ የሚሆን 350 ሺህ እንዲከፍሉለት በሚል እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡
ይሁን እንጂ ወጣቱ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የወረታ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ኢ/ር አግማስ ጌቴ ወጣቱ ድርጊቱን የፈጸመው ሆን ብሎ ገንዘብ ለማግኘት በመፈለግ ነው ብሏል፡፡
ቤተሰቦቹ እና ፖሊስ አድርገውታል በተባለ ክትትል ወጣቱ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ኢ/ር አግማስ ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪው በሰጠው የእምነት ቃልም አጎቱ ሃብታም ስለሆነ ከእሱ ገንዘብ ለመቀበል ሲል የተጠቀመው የማጭበርበር ስልት መሆኑን መግለጹን ፖሊስ አስታውቋል፡፡