ተመድ በግጭቱ ለተጎዱ በ3 ክልሎች ለሚገኙ 9550 አባዎራዎች ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ
ተመድ ባለፉት ጥቂት ቀናት በትግራይ ክልል ያለው የእርዳታ ተደራሽነት ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ብሏል
ተመድ በትግራይም ሆነ በሌሎች ክልሎች ያለው የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱን ገልጿል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የስደተኞች ኤጀንሲ/ዩኤን ኤች ሲ አር/ በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡
ላለፉት 8 ወራት በትግራይ ክልል እየተካሄደ የቆየው ግጭት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን የገለጸው ኤጀንሲው፤ አሁን ላይ በአማራ ክልል ደባርቅ ብቻ 40 ሺ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ከአከባቢው ባለስለጣናት ለማወቅ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ከባድ በመሆኑ አስቸኳይ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አመላክቷል ጀንሲው፡፡
እሰካሁን 1ሺ800 ለሚሆኑ አባዎራዎች (4ሺ 600 ሰዎች) ድጋፍ መደረጉንም ነው በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች የገለጹት፡፡ ቃል አቀባዩ “አሁን ላይ በአማራ እና አፋር ክልሎች ያለውን መፈናቀል ዩኤን ኤች ሲ አር እጅጉን ያሳስበዋል” ሲሉ ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት በትግራይ ክልል ያለው የእርዳታ ተደራሽነት ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ በክልሉም ሆነ በሌሎች ክልሎች ያለውን የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱንም ተናግሯል ቃል አቀባዩ፡፡
“ዩኤን ኤች ሲ አር በመቀሌ፣ሽረ እና አፋር ክልል ለሚገኙ 7 ሺ 750 አባዎራዎች የብረድ ልብስ፣፣ ባልዲ፣ ሳሙና ፣ የወጥ ቤት ቁሳቁሶች እና የትንኝ መረቦች እርዳታ አድርገዋል”ም ብሏል ክሬቨንኮቪች ፡፡
ኤጀንሲው አሁን በየትምህርት ቤቶች ተጠለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚሆኑና እስከ መስከረም አጋማሽ የሚጠናቀቁ አዳዲስ መጠለያ ጣብያዎች እየገነባ መሆኑንም ክሬቨንኮቪች ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ በጊዜ ሂደት እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት እስካሁን ተደራሽ ያልሆኑ እና አርዳታ ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ግጭት የሰው ልጆች ሲቃይ ከመጨመር እና ለተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶች ከመዳረግ ባለፈ ምንም ፋይዳ የለውም ያሉት ቃል አቀባዩ “ግጭቱ ማስቆም የግድ ነው”ም ብሏል፡፡
ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህጎች ተገዢ በመሆን የንጹሃን ዜጎች እንዲጠብቁም አሳስቧል፡፡
በትግራይና ሌሎች ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሻለና አመቺ ሁኔታ እንዲኖር ሁሉም ኃይሎች የድርሻቸው እንዲወጡም ክሬቨንኮቪች ጠይቋል፡፡
በጥቅምት ወር 2013 የህወሓት ሃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጀው “ህግ ማስከበር ዘመቻ” ተጀመረው ግጭት አሁን ላይ 11 ወራት ሊሆነው ነው፡፡
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ሃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምረው በርከታ ቦታዎች መቆጣጠር ችለዋል፡፡
ትግራይን የተቆጣጠሩት የትግራይ ሃይሎች፤ ወደ አጎራባችና አማራና አፋር ክልል ጥቃት ከፍተው ቦታዎች ተቆጣጥረዋል፡፡
የህወሓት ኃይሎች ወደ አጎራባቸው ክልሎች ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስትና የፌደራል መንግስት የህወሓት ሃይሎችን ለመዋጋት የዘመቻ ጥሪ አቅርበዋል፤ጦርነትም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የህወሓት ሃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በማድረሳቸው ከ300ሺ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውንና የተናጠል ተኩስ አቁሞ የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም ያለው የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊትና የክልል ልዩ ሃይሎች ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን መግለጹ ይታወሳል፡፡