በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እንግሊዛዊያን ኑሮ ተወደደብን በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ
እንግሊዝን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ዜጎች የዋጋ ግሽበት አጋጠመ በሚል መንግስታቸውን በመጠየቅ ላይ ናቸው
ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ በለንደን የፈጣን ባቡር አገልግሎት ተቋርጧል
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እንግሊዛዊያን ኑሮ ተወደደብን በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ፡፡
ከተጀመረ አራት ወራትን ባስቆጠረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የኑሮ ውድነት ገፈትን መቅመስ ከጀመሩ አህጉራት መካከል አውሮፓ ቀዳሚው ነው፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በዓለም ላይ የነዳጅ እና ምግብ ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን አውሮፓዊያን ደግሚ ከተጎጂዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በእንግሊዝም ጦርነቱን ተከትሎ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተከሰተባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን የኑሮ ውድነቱ ባለፉት 30 ዓመታት ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች መንግስታቸው ለኑሮ ውድነቱ ማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስድ በሰላማዊ ሰልፍ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ የባቡር ጣቢያ ሰራተኞች ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሲሆን በዛሬው ዕለት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት በለንደን የምድር ውስጥ ፈጣን ባቡር አገልግሎት ተቋርጧል ተብሏል፡፡
በዚህም ምክንያት ተሳፋሪዎች የተጉላሉ ሲሆን ሁኔታው በጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አስተዳደድር ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ ሰራተኞች ማህበር ለመምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የቆሻሻ ማስወገድ እና ፍሳሽ አገልግሎት ሰራተኞች እና ሌሎች ሙያተኞች መንግስት የዋጋ ቅነሳ ድጎማ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኮሮና ቫይረስ የተጎዳው የአውሮፓ ኢኮኖሚ ሳያገግም ወደ ተባባሰ ችግር ሊስገባው እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለካቢኔ አባላቶቻቸው ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ሰልፎች ሁሉ አላስፈላጊ እና ስህተቶች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዋጋ ግሽበቱን ተከትሎ በአውሮፓ ትላልቅ ከተሞች ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ሲሆኑ በብራስልስ አየር መንገድ ሰራተኞች ለሰዓታት ስራ አቁመው የነበረ ሲሆን የጀርመን መንግስት ለሰራተኞች በሰዓት የሚሰጡ ክፍያዎች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ተገዷል፡፡