አመራሮቹ የትምህርት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እና የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር በመሆን ነው የመንግስት ካቢኔን በአባልነት የተቀላቀሉት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተቃዋሚነት የሚፎካከሩ ሶስት ፓርቲዎች አመራሮችን የካቢኔያቸው አባላት አደረጉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ነው የካቢኔያቸው አባላት ያደረጉት፡፡
እንደ አዲስ የተዋቀሩት አዳዲስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የትኞቹ ናቸው?
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፤ ቃለ መሃላም ፈጽመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላቱ በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነቶች ላይ እንዲሠሩ የሚያስችለውን ውሳኔ ከሰሞኑ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንትን ኮሚሽነር ሆነው ርክክብ አድርገዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሐመድ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የንቅናቄው ምክትል ሊቀመንበር የሱፍ ኢብራሂም የአዲስ አበባ ከተማ ንብረት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በመሆን መሾማቸው ይታወሳል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የኦሮሚያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸውም አይዘነጋም፡፡
በቅርቡ ሁሉን አካታች የሆነ ብሄራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚጀመር ጠ/ሚ ዐቢይ ተናገሩ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀረቡ 22 ሚኒስትሮች ሹመት በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆም ሚኒስትሮቹ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡