ህወሓት ባካሄደው አወዛጋቢ ጉባኤ ዶ/ር ደብረጽዮንን በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ
ጉባኤው በአቶ ጌታቸው ምትክ አቶ አማኑኤል አሰፋን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን አስታውቋል
ጉባኤው ተቃውሞ ሲያቀርቡ የነበሩትን አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን በአዲስ ተክቷቸዋል
ህወሓት ባካሄደው አወዛጋቢ ጉባኤ ዶ/ር ደብረጽዮንን በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን አስታውቋል።
በምርጫ ቦርድ እና በበርካታ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ የተነሳበትን ተቃውሞ ወደ ጎን በመተው 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤውን ያካሄደው የህወሓት ቡድን ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን አስታውቋል።
በዶክተር ደብረጽየን የሚመራው ህወሓት "የመዳን ጉባኤ"ሲል የሰየመውንጉባኤ በዛሬው እለት ማጠናቀቁን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
ጉባኤው እንዳይካሄድ ሲቃወሙ የነበሩት አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት በአዲስ ተተክተዋል።
መግለጫው አቶ አማኑኤል አሰፋ በአቶ ጌታቸው ቦታ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፣ አቶ ገብረ ካህሳይ እና ብርሃነ ከበደ የቁጥጥር ኮሚሽኑ ዋናና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል ብሏል።
አንጋፋ የሆነው የትግራይ ፓርቲ ህወሓት ውስጥ ክፍፍል የተፈጠረው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በአመጽ ተሳትፏል በሚል ህጋዊ ሰውነቱ የተሰረዘበት ህወሓት በድጋሚ ህጋዊ ሰውነቱን ለማስመለስ በተደረጉ ሂደቶች ጉዳይ ነው።
ህወሓት የምርጫ ቦርድን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በመተው ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄደ ጀመረ
የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ እና የስነምግባር አዋጅ መሰረት፣ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ወስኗል።
ይህ ውሳኔ በዶክተር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት ህጋዊ ሰውነቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስለት እንጂ "በልዩ ሁኔታ" እንዲመዘገብ እንደማይፈልግ እና እንደማይቀበለው ግልጽ አድርጓል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት እና በህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው የሚመራው ቡድን ደግሞ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት ለማስመለስ ለምርጫ ቦርድ የገቡት ሰነዶች ማዕከላዊ ኮሚቲው የማያውቃቸው ናቸው ሲል ነው የተቃወመው።
ይህን ተከትሎ ነበር አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸውን ከጉባኤው ማግለላቸውን ባወጡት የጋራ መግለጫ ይፋ ያደረጉት።
ምርጫ ቦርድም ከፈቃዱ ውጭ ለሚደረግ ጉባኤ እና በጉባኤዎ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ ቢገልጽም፣ በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በአቋሙ ገፍቶበት ጉባኤውን አካሃዶ ዛሬ አጠናቋል።
በአቶ ጌታቸው የሚመራው ቡድን በዛሬው እለት ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የትግራይ የጸጥታ ኃይል በተፈጠሩ ልዩነቶች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ እና በዶክተር ደብረጺዮን የሚወራው ጉባኤ ለሚያሳልፈው ጉባኤ እውቅና እንደማይሰጥ ገልጿል።
በሌላ በኩል በትግራይ ያለው ክፍፍል እንደሚያሳስባቸው የገለጹት በትግራይ የሚንቀንሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትግራይ አካታች መንግስት ማቋቋም ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ለገሰ ቱሉ ጉባኤው በተጀመረበት ወቅት በፌስ ቡክ ገጻቸው ህወሓት የፌደራል ተቋማትን ባለማክበር በተደጋጋሚ ስህተት እየሰራ ነው የሚል ጠንካራ ትችት መሰንዘራቸው ይታወሳል።