“ህወሓት በማካሄድ ላይ የሚገኝው ጉባኤ ትግራይንና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም” - አቶ ጌታቸው ረዳ
የህወሓት ም/ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው “ስብሰባው ለጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የሚንቀሳቀስ አካል የሚያደርገው ነው ብለዋል
“ህወሓት እንደመሸሸጊያ የሚያነሳው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግዴታ ዛሬ በተጨባጭ ተግባር ደምስሶታል”- ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲው ዛሬ ማካሄድ የጀመረው ጠቅላላ ጉባኤ ትግራይን እና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም ሲሉ ተናገሩ።
ህወሓትምርጫ ቦርድን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ሲደርሱት የነበሩትን ማስጠንቀቂያዎችን ወደ ጎን በመተተው "የመዳን ጉባኤ" ሲል የሰየመውን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ማካሄደ ጀምሯል።
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸውን ያስታወቁት ቀደም ብለው ነሃሴ 2፣2016 ዓ.ም ለህወሓት ሊቀ መንብር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) እና ለፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ መንበረር አቶ ተክለብርሃን አርአያ በጻፉት ደብዳቤ ነበር።
በዛሬው እለት ባወጡት መግለጫ ደግሞ “የህወሓት ጉባዔ በችኮላና የጋራ መግባባት ሳይደረስበት፤ በማደናገርና በአቋም አልባነት አሰባስበናቸዋል በሚሉት ኔትወርክ ተቃዋሚ ናቸው የሚባሉ የተወሰኑ አመራሮች ለማስወገድ አለማ አድርጎ የሚካሄድ ነው” ብለዋል።
“ድርጅቱ ጉባኤ ማካሄዱን የሚቃወም አካል የለም” ያሉት አቶ ጌታቸው ነገር ግን “ጉባኤው በህወሓት ታሪክ ፣ የትግራይ ህዝብ ትግል በጠራ ስልትና ታክቲክ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በሰከነ መንገድ እንዲደረግ ስንጠይቅ መሰንበታችን ይታወቃል” ነው ያሉት።
ስለሆነም ጉባኤዎቻችን በትግራይና በህዝቦቿ ላይ እየተጋረጡ ያሉ ፈተናዎችን ለማሸነፍ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አቅጣጫን እንድንለይ በሚያስችሉ መልኩ መደረግ ሲኖርባቸው በመካሄድ ላይ የሚገኝው ጉባኤ ለጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የሚንቀሳቀስ አካል የሚያደርገው ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
አክለውም የተሻሻለው የፓለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ህወሓት እንደ አዲስ እንደሚዘገብ የሚያደርግ ፣ ወርቃዊው የትግራይ ህዝብ ትግል የሚያጎድፍ በቀጣይ ቅርቃር ውስጥ የሚከት መሆኑን በመገንዘብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ በማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የተደረሰው መግባባትና መተማመን ወደ ጎን በመተው “ከፌደራል መንግስት ጋር ተማምነናል” በሚል ማደናገሪያ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመነጋገር ከማእከላዊ ኮሚቴ እና ካድሬ በመደበቅ የተሄዴበት ሂደት ወዳልተፈለገ ወጥመድ እንድንገባ አድርጎናል ሲሉ በመግለጫቸው አመላክተዋል።
አክለውም በዚህ ምክንያት ለሚፈጠር ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂው ለጠባብ ቡድናዊ ፍላጎቱ ብቻ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ነው ብለዋል።
የህዝቡ ሰላም እንዳይደፈርስና እንዳይረበሽ ከህዝባችንና ከመላ አባላቶቻችን ጋር በመሆን በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
መላውን የትግራይ ህዝብና አቅማችንን በማስተባበር፣ የተደራጀ ትግል እና ከፍተኛ የፖለቲካ ድርድር በማድረግ ድርጅታችን ህወሓት ህጋዊ እውቅና እንዲሰጠው በማድረግ የትግራይን ሙሉ በሙሉ ማገገምና ማደግ እናረጋግጣለን ሲሉ ምክትል ሊቀመንበሩ ባወጡት መግለጫ ላይ ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ህወሓት ደጋግሞ እንደመሸሸጊያ የሚያነሳው የፕሪቶሪያ ስምምነት የፌደራል ተቋማትን አሰራሮች፣ ህጎችና አካሄዶች በጥብቅ ሊያከብር ግዴታ ጥሎበታል ብለዋል።
ነገር ግን “ቀድሞ የገባውን ግዴታ ሲሸራርፍ የመጣው ህወሓት ዛሬ በተጨባጭ ተግባር ደምስሶታል” ብለዋል ሚኒስተሩ።
የህወሓት የትግራይ ህዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል” ያሉት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ “አንዴ፡ ሁለቴ፡ መሳሳት ያለንና የነበረ ነው፤ በተመሳሳይ መንገድ: ተመሳሳይ ስህተት ሶስቴ መፈጸም ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ብቻኛው ተጠያቂ እራሱ ይሆናል” ሲሉ ገልጸዋል።