የትግራይ ፓርቲዎች የአደራዳሪውን ኦባሳንጆን ንግግር ተቃወሙ
ፓርቲዎቹ በፕሪቶሪያው ስምምነት አወዛጋቢ የተባሉት ቦታዎች በገለልተኛ አካል ይተዳደሩ ያሉትን ኦባሳንጆን ተቃውመው መግለጫ አውጥተዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/243-151833-img-20250218-wa0025-1-_700x400.jpg)
ፓርቲዎቹ የፌደራል መንግስት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ እንጂ ገለልተኛ አካል አይደለም ብለዋል
የትግራይ ክልል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፕሪቶሪያው ስምምነት አደራዳሪ የሆኑት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ያደረጉትን ንግግር ተቃወሙ፡፡
ፓርቲዎቹ የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በሚገመግመው ስብሰባ ላይ "የትግራይ መሬቶችን" አስመልክቶ ያደረጉትን ንግግር ነው የተቃወሙት፡፡
ኦባሳንጆ ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩና በፕሪቶሪያው ስምምነት አወዛጋቢ የተባሉት ቦታዎች "በገለልተኛ አካል" ቁጥጥር ስር መሆን እንደሚገባቸው ሀሳብ መስጠታቸውን ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
ስምምነቱ አወዛጋቢ የተባሉትን ቦታዎች በስም ባይጠቅስም የአማራና ትግራይ ክልሎች የሚወዛገቡባቸው የድንበር አካባቢዎች ጉዳይ በህገመንግስቱ መሰረት መፈታት እንዳለበት ጠቅሷል።
ቦታዎቹ በትግራይ በኩል ምዕራብ ትግራይ እና ደቡባዊ ትግራይ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን በአማራ ክልል ደግሞ ወልቃይትና ራያ የሚል ስያሜ አላቸው። እነዚህ ቦታዎች ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩ ቢሆንም ቀደም ሲል በአማራ በኩል የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ሲነሳባቸው ቆይቷል።
የፌደራል መንግስት ቦታዎቹን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ በህገመንግስቱ መሰረት በህዝበ ውሳኔ እንዲካለሉ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል።
ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አደራዳሪው መሬቶቹ በገለልተኛ አካላት ስር ይሁኑ ማለታቸው የፌደራል መንግስቱን ለማለት ፍለገው ነው ያለ ሲሆን፤ “ነገር ግን የፌደራል መንግስት የፕሪቶሪያው ስምምነት አንድ አካል እንጂ ገለልተኛ አይደለም” ሲል ተቃውሟል፡፡
በተጨማሪም “የትግራይ ተወላጆቹ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉባቸው እነዚህ መሬቶች አሁንም በፌደራል መንግስት እና በአጋሮቹ የተያዙ ናቸው” ያለው መግለጫው በዚሁ መቀጠል እንደሌለበት አሳስቧል፡፡
“የአደራዳሪው ኦባሳንጆ ሀሳብ በቀጥታ የፕሪቶሪያ ስምምነት መንፈስ እና ድንጋጌዎች ይቃረናል፣ይህም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለሱን እንደ አንድ መሠረታዊ ምሰሶ በግልጽ ያስቀምጠውን የስምምነት ሀሳብ በግልጽ የሚጥስ ነው” ብሏል የሳልሳይ ወያኔ መግለጫ፡፡
በስምምነቱ መሰረትም የፌደራል መንግስቱ የትኛውንም የክልሉን መሬት ይዞ እንዲቀጥል የሚጠቅስ ነጥብ ባለመኖሩ ሀሳቡ ከህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረስ ነው ሲል አመላክቷል፡፡
በዚህም የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የአዳራዳሪነት ሚና ያላቸው አካላት ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተሉት እና ማብራርያ እንዲሰጡበት ፓርቲው ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ባይቶና እና ዓረና) በጋራ ባወጡት መግለጫ ንግግሩን የኮነኑት ሲሆን፤ “የትግራይ ህዝብ በገዛ መሬቱ ያለውን መብት የሚጋፋ ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
“ኦባሳንጆ በፌደራል መንግስት እና በህውሓት መካከል እንደ አደራዳሪ አካል ገለልተኛ አቋም ማንጸባረቅ ሲገባቸው በግምገማው ላይ ያንጸባረቁት ሀሳብ ግን ከፌደራል መንግስት ጋር መወገናቸውን ያመላከቱበት ነው” ብሏል የፓርቲዎቹ መግለጫ፡፡
መግለጫው ሲቀጥል፡- “የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና አላማ በትግራይ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ወደነበረበት መመለስ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች በሰላም እንዲመለሱ እና በትግራይ እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ሆኖ ሳለ፤ የኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አስተያየት በተቃራኒው የተነገረ ውጥረቱን የሚያባብስ እና የህዝባችንን ስቃይ የሚያራዝም ነው” ብሏል፡፡
“የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ስህተት እንዲደገም አይፈቅድም” ያለው መግለጫው የትግራይ መሬቶችን በሌላ አካል ቁጥጥር ስር እንዲቆይ ጉዳዩን ህጋዊ ለማስመሰል የሚደረግ ማንኛውም ጥረት እንደሚቃወም አስቀምጧል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈራሚ የሆነው ህውሓት እስካሁን አደራዳሪው ሰንዝረውታል በተባለው ሀሳብ ዙሪያ ይፋዊ መግለጫ አላወጣም፡፡