ሀገራቱ የሚፈራረሙት ስምምነት በቀጣናው ሁለንተናዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እስራኤል ታሪካዊውን ስምምነት በዋሽንግተን ዛሬ ይፈራረማሉ
ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ በአረብ ሀገር እና በእስራኤል መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ግንኙነቶችን መደበኛ ለማድረግ ታሪካዊ ስምምነት ከተደረሰ ከሳምንታት በኋላ ዛሬ ማክሰኞ በዋሽንግተን በሚካሄድ ሥነ-ስርዓት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከእስራኤል ስምምነታቸውን ለማጽናት ይፈራረማሉ፡፡
በስምምነቱ መሰረት የተያዙትን የፍልስጤም ግዛቶች ለማጠቃለል ያቀደችው እቅድ እንዲቆም ተስማምታለች ፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ በኤምሬትስ እና እስራኤል መካከል የሚደረገውን የስምምነት ፊርማ ለመፈረም ሀገራቸውን ወክለው እሁድ ምሽት ዋሽንግተን ገብተዋል፡፡
ሼክ አብዱላህ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ማክሰኞ በዋይት ሃውስ በሚደረገው የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ እንዲሳተፉ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መጋበዛቸውን ተከትሎ ነው ሚኒስትሩ ዋሽንግተን ያቀኑት፡፡
“ስምምነቱ የዩኤኢን የውሳኔ ሰጭነት እና ጥቅሟን የማስጠበቅ አቅም ወዳጆቿም ይሁን ጠላቶቿ በአግራሞት እንዲገነዘቡ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው” ሲሉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የባህል ጉዳዮች እና የህዝብ ዲፕሎማሲ ረዳት ሚኒስትር ኦማር ጎባሽ ተናግረዋል፡፡ ኦማር ጎባሽ በሼክ አብዱላህ የሚመራው የዋሽንግተን ከፍተኛ ልዑክ አካል ናቸው፡፡
ረዳት ሚኒስትሩ ጎባሽ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት በሶስተኛ አካል ታደርግ እንደነበር ገልፀው “ይህ ግን አሁን ተቀይሯል” ብለዋል፡፡ “እኛ የራሳችንን ሉዓላዊነት የምናከብር ሀገር ነን” ስለማለታቸውም ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ላይ የደረሰችው ባህሬንም እንዲሁ ዛሬ በዋሽንግተን የራሷን የሰላም ስምምነት ትፈርማለች፡፡
ባህሬን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እ.ኤ.አ. በ 1979 እና በ 1994 ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነቶችን ከፈረሙት ግብፅ እና ዮርዳኖስ በተለየ ከእስራኤል ጋር ጦርነት አላካሄዱም፡፡
“በሰላም ምትክ ሰላምን ለማግኘት እየተጓዝኩ ነው ፤ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ሁለት የሰላም ስምምነቶች ላይ ደርሰናል” ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እሁድ አመሻሽ ላይ ወደ ዋሽንግተን ጉዞቸውን ሲጀምሩ በትዊተር ገፃቸው ጽፈዋል፡፡
“ይህ አዲስ ዘመን ነው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ዲፕሎማሲያዊ ሰላምን ከኢኮኖሚ ሰላም ጋር አንድ የሚያደርጉ ሲሆን የሚቆጠሩ በኢንቨስትመንቶች ፣ በትብብር እና በጋራ ጥረት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚያችን ያስገባሉ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሀገራቱ በኢኮኖሚ ፣ ፖለቲካ ፣ ቴክኖሎጂ ፣ ማህበራዊ ፣ ቱሪዝም ፣ ባህል እና ሌሎችም መስኮች ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡