አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 14 የሚሆኑ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ህወሓት ከሚያካሂደው ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው እሁድ ነበር
ህወሓት የምርጫ ቦርድን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በመተው ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄደ ጀመረ።
አንጋፋው የትግራይ ፖርቲ ህዝበ ወያኔ ሀርነት ትግራይ(ህወሓት) "የመዳን ጉባኤ" ሲል የሰየመውን ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄደ ጀምሯል።
ፓርታው በፌስ ቡክ ገጹ የህወሓት አርማ የያዙ ተሰብሳቢዎች አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው የሚያሳይ ምስል ለቋል።
ፓርቲው ስብሰባውን እያካሄደ ያለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ማሳሰቢያ እና በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበውን ተቃውሞ ወደ ጎን በመተው ነው።
አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 14 የሚሆኑ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ህወሓት ከሚያካሂደው ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው እሁድ እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ ነበር።
አባላቱ በተወሰነ ቡድን "ህወሓትን ለማፍረስ በሚደረግ ጉባኤ" እንደማይሳፉ ገልጸዋል።
መግለጫውን ያወጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጌታቸው ረዳ፣በየነ መክሩ፣ክንደያ ገብረህይወት፣ ሀጎስ ጎደፋይ፣ሰብለ ካህሳይ፣ ብርሃን ገብረየሱስ፣ ሰለሞን ማዓሾ፣ ሺሻይ መረሳ፣ ሀብቱ ኪሮስ፣ ረዳኢ ሀለፎም፣ ነጋ አሰፋ፣ ገብረህይወት ገብረእግዝሄር፣ ሩፋኤል ሽፈሬ፣ ርስቁ አለማው ናቸው።
አባላቱ ላለመሳተፍ አቋም የያዙት ፓርቲው ከአሰራር ውጭ ጉባኤ ለማድረግ በማቀዱ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸውን ያስታወቁት ቀደም ብለው ነሃሴ 2፣2016 ዓ.ም ለህወሓት ሊቀ መንብር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) እና ለፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ መንበረር አቶ ተክለብርሃን አርአያ በጻፉት ደብዳቤ ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ማታ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎችን አለማሟላቱን ገልጾ፤ ጉባኤውን እንዳያካሄድ አሳስቦ ነበር።
ህወሓት የጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አይችልም - ምርጫ ቦርድ
ቦርዱ፣ ፓርቲው ጉባኤ ከማካሄዱ ከ21 ቀናት በፊት ለቦርዱ ማሳወቅ እና የቦርዱ ታዛቢዎች በጉባኤው እንዲገኙ ማድረግ ጉባኤ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን ጠቅሷል በመግለጫው። ህወሓት የቦርዱን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በመተው ጉባኤውን ካደረገ፣ ለጉባኤው እና በጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ ቦርዱ አሳስቦ ነበር።
ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የሞርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር ማሻሻያ አዋጅ መሰረት፣ በልዩ ሁኔታ በፓርቲነት መዝግቦታል።
ህወሓት የጠየቀው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ቢሆንም፣ ቦርዱ በአዋጁ ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል የህግ አስራር የለም በማለት አልተቀለውም።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸውም ቢሆኑ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ሰነድ ከማዕከላዊ ኮሚቴው እውቅና ውጭ የሚል ተቃውሞ አሰምተዋል።
ህወሓት በፕሬቶሪያው የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ቢጠይቅም፣ የፌደራል መንግስት ከምዝገባ እና ህጋዊ ሰውነት ማስመለስ ጋር የተያያዘ ግዴታ እንዳልገባ ገልጿል።