መንግስት የህወሓትን የሕግ ሰውነትና የምዝገባን በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት “የወሰድኩት የተለየ ግዴታ የለም” አለ
ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ ውሳኔ አሳልፏል
ህወሓት “ከፕሪቶሪያው ስምምነትና ከህግ አንፃር ህጋዊ ሰውነቴ ይመለስ ነው ያልኩት” በሚል የምርጫ ቦርድ ውሳኔን አልቀበልም ብሏል
የፌዴራል መንግሥት የህወሓትን የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ እንደሌለ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው አርብ ነሃሴ 3 2016 ዓ.ም በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ መሠረት ለህወሓት የምዝገባ ምስክር ወረቀት መስጠቱን ገልጧል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ህወሓት የጠየቀው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መሆኑን እና በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ ውሳኔ ማሳለፉን መግለጹ ይታወሳል።
ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ላቀረበው የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ እንደማይቀበል እና በፕሪቶሪያው ሰምምነት መሰረት ጥያቄው እንዲታይለት ጠይቋል።
ይህንን ተከትሎም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ መሠረት ለህወሓት የምዝገባ ምስክር ወረቀት ለመስጠት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚቀበል አስታውቋል።
“የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ የገባው ግዴታ የህወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንዲነሣ ሂደቱን የማሣለጥ ኃላፊነት ነው” ያለው መግለጫው፤ የፌዴራል መንግሥት የህወሓትን የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ እንዳለነበረም አስታውቋል።
ህወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 7 (1) (A) መሠረት የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት፣ ሕጎች፣ የፌዴራል ተቋማትን እና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ሥልጣን የማክበር ግዴታ መግባቱንም መንግስት በመግለጫው አስታውቋል።
“ስለዚህ ህወሓት የሀገሪቱን የፖለቲካ ፖርቲዎች የምዝገባ ሕግ እና የምርጫ ቦርድን ሥልጣን በማክበር የመሥራት ግዴታ እንዳለበት ግልጽ ነው” ያለው መንግስት፣ “ከፕሪቶሪያ ስምምነት አኳያም ሲታይ የህወሓት የሕግ ሰውነት ጉዳይ አግባብነት ባለው ሕግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው” ብሏል።
የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከህወሓት አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ምክክሮችን በማድረግ፣ ህወሓት እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖረው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም አመላክቷል።
መንግስት ህወሓትም ሆነ ሌሎች የትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቡድኖች ወደ ሕጋዊ መሥመር ሊመጡ የሚችሉበትን መንገድ የሚያመቻች የሕግ ማሻሻያ ማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ መጽደቁን አስታውሷል።
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ፣ በተሻሻለው የአዋጁ ድንጋጌ መሠረት የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ከመንግሥት በኩል ሊደረግ የሚችለው ሁሉ ተደርጓል ብሏል መግለጫው።
የፌዴራል መንግሥት ከግማሽ ርቅት በላይ ሄዶ፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ከሚጠበቅበት እና ካለበት ግዴታ አልፎ ከምርጫ ቦርድ እና ከህወሓት ጋር በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ውይይቶች ማድረጉንም አመላክቷል።
ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና ለማግኘት የሚጠበቅበት የፓርቲ ሰነዶቹን ማለትም የፓርቲውን ፕሮግራም እና ሕገ ደንብ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሰነዶችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት ማገኘቱነም መንግስት አስታውቋል
ስለሆነም የምዝገባ እና የህግ ሰውነትን ጉዳይ በዚህ በመቋጨት፤ የሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ፣ ሰላምን በማጽናት፣ በመልሶ ግንባታ እና በልማት አጀንዳ ላይ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ጠየቀው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መሆኑን እና በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ ውሳኔ ማሳለፉን መግለጹ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ላቀረበው የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ እንደማይቀበል አስታውቆ መግለጫ አውጥቷል።
ህወሓት በመግለጫው ያቀረብነው ጥያቄ ከፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ከህግ እና ህወሓት እያደረገ ካለው ተጨባጭ እንቅስቃሴ አንፃር የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚል ብቻ ነው ብሏል።
በሌላበኩል የትግራይ ጊዜያው አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታው ረዳ ለምርጫ ቦርድ በላኩት ደብዳቤ “በህወሓት ስም ለምዝገባ የቀረበው የቀረበው ማመልከቻ ማዕከላዊ ኮሚቴው የማያውቀው ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው “ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለነዝህ ግለሰቦች የሰጠው ምዝገባ በተጭበረበረ ማስረጃ መሰረት የተሰጠ በመሆኑ መልሶ እንዲመረምረው እንጠይቃለን” ብለዋል።