ህወሓት በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ስወያይ ነበር አለ
መንግስት በቅርቡ የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ክስ በማቋረጥ ከእስር መልቀቁ ይታወሳል
ደብረ ጽዮን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር) በሌሎች መንገዶች ከመንግስት ጋር ስናደርግ በነበረው ውይይት ውጤቶች ተገኝተዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል
በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ሲወያይ እንደነበር ህወሓት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር) በሌሎች አካላት በኩል ከመንግስት ጋር ሲወያዩ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
በውይይቶቹ ውጤት መገኘቱንም ነው ዶ/ር ደብረ ጽዮን የገለጹት፡፡ አሁንም ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔዎችን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር የታሰበ ምንም ዐይነት ድርድር እንደሌለ ሲገልጽ ሰንብቷል፡፡
ሆኖም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከዳያስፖራዎች ጋር በነበራቸው ውይይት መንግስት ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር ተናግረዋል የሚሉ አንዳንድ ዘገባዎች ነበሩ፡፡
ከሰሞኑ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ከዘገባዎቹ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “መንግስት እስካሁን ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር እንደሚደራደር አላሳወቀም” ብለዋል።
መንግስት አሁንም ቢሆን ህወሓትን በሽብርተኝነት ነው የሚመለከተው ያሉት አምባሳደር ዲና ድርድር ሊደረግ ነው የሚለው መረጃ ትክክል አለመሆኑን እና ከመንግስት በኩል የወጣ አለመሆኑንም አያይዘው መግለጻቸውን አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል።
መንግስት በቅርቡ ክስ በማቋረጥ የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከእስር መልቀቁ አይዘነጋም፡፡