ቱርክ በደህንነት ስጋት ምክንያት ዘጠኝ የምዕራባውያን አምባሳደሮችን ጠራች
ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎችን ለጊዜው ለመዝጋት እና የጸጥታ ማስጠንቀቂያዎችን ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው አንካራ ጥሪውን ያቀረበችው
ባለፉት ሳምንታት በስዊድን፣ ዴንማርክ እና ፊንላንድ ቅዱስ ቁርዓን መቃጠሉ በቱርክ ቁጣን ተቀስቅሷል
ቱርክ በደህንነት ስጋት ምክንያት ዘጠኝ የምዕራባውያን አምባሳደሮችን ጠራች
ቱርክ የአሜሪካ እና የስዊድንን ጨምሮ የዘጠኝ ምዕራባውያን ሀገራት አምባሳደሮችን ጠርታለች።
ቱርክ ይህን እርምጃ የወሰደችው በአውሮፓ ቁርአን መቃጠሉን ተከትሎ ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎችን ለጊዜው ለመዝጋት እና የጸጥታ ማስጠንቀቂያዎችን ማውጣታቸውን ለመተቸት ነው ተብሏል።
የቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዘርላንድ እና ብሪታንያ ልዑኮቻቸውን መጥራታቸውን በአንካራ የሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ምንጮች ገልጸዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በስዊድን፣ ዴንማርክ እና ፊንላንድ ቅዱስ ቁርዓን በአክራሪ ፖለቲከኞች ተቃጥሏል።
የአውሮፓ ሀገራት ድርጊቱን ቢያወግዙም፤ አንዳንዶች የነጻ ንግግር ህጎች በመጥቀስ መከላከል እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ምዕራባዊያን ሀገራት ባለፈው ሳምንት በቱርክ በተለይም በዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች እና ሙስሊም ባልሆኑ የአምልኮ ቦታዎች ላይ ለዜጎቻቸው ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ከእነዚህ ሀገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና አሜሪካ ይገኙበታል።
በዚህ ሳምንት ለደህንነት ሲሉ በቱርክ የሚገኙ ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮኖችን ለጊዜው ከዘጉ ሀገሮች መካከል ደግሞ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድ ይገኙበታል ተብሏል።
አንዳንዶቹ ማዕከላዊ የኢስታንቡል አካባቢዎችን በመጥቀስ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸውን ቦታዎች ጠቅሰዋልም።
የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ሱሌይማን ሶይሉ በትዊተር ገጻቸው ኤምባሲዎቹ በቱርክ ላይ “አዲስ የስነ-ልቦና ጦርነት” እያካሄዱ ነው ብለዋል።
ስዊድን እና ፊንላንድ ባለፈው ዓመት ለኔቶ ለአባልነት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ከቱርክ "ያልተጠበቀ" ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።