የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፀጥታ ችግር ያሳለፉትን ጊዜ ማየታቸው ወታደር ለመሆን እንዳስወሰናቸው ገልጸዋል
የኢፌዴሪ መከላከያ ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን ምልምል ወታደሮች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ከዛሬ ተመራቂዎች መካከል ደግሞ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዲግሪ ከተመረቁ በኋላ መከላከያን የተቀላቀሉ ሁለት መንትዮች ይገኛሉ፡፡
መንትዮቹ መሰረታዊ ወታደር ጌታሁን ዋሴ እና መሰረታዊ ወታደር በለጠ ዋሴ ይባላሉ።
ጌታሁን በወለጋ ዪኒቨርሲቲ በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ፤ በለጠ ደግሞ በአልፋ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግና ፋይናንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
ከትምህርታቸው መጠናቀቅ በኋላ በጉጉት ይጠብቁት የነበረው የመከላከያን የቅጥር ማስታወቂያ ብቻ እንደነበር መንትዮቹ ተናግረዋል።
"የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በፀጥታ ችግር ያሳለፉትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስብ ከተመረቅን በኋላ ወታደር ለመሆን ወሰንን" ሲሉ ውትድርናን የመረጡበትን ምክንያት ይገልጻሉ፡፡
"ትናንትን ስናስበው ፣ እናትና አባት በድህነት አሳድገው ለቁም ነገር ይደርሱልኛል ያሏቸው ወጣቶች ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በፀጥታ ችግር ህይወት የከፈሉበት ነው" የሚሉት መንትዮቹ "የፀጥታ ችግሮች እናት በስስት የምታየው ልጇን ትምህርት ቤት ልካ እስከወዲያኛው ያጣችበት ነው" ሲሉ ቁጭታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ስለሆነም "የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ያሳለፉትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስበው የፀጥታ ችግር የነበረበት በመሆኑ ፣ ለወገኖቻችን ችግር ለመድረስ ከተመረቅን በኋላ ወታደር ለመሆን ወሰንን" ብለዋል።
ጦላይ ማሰልጠኛ እነኚህን መንትዮች ጨምሮ በፍላጎታቸው ሠራዊቱን የተቀላቀሉ በርካታ መሰረታዊ ወታደሮችን ዛሬ ማስመረቁን መከላከያ ሠራዊት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
ከጦላይ በተጨማሪ ሁርሶ እና ብርሸለቆ በሚገኙ የወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ መሰረታዊ ወታደሮችም በየማሰልጠኛ ማዕከሉ በዛሬው ዕለት መመረቃቸውንም ነው ሠራዊቱ የገለጸው፡፡