አሜሪካ እና የእርዳታ አጋሮቿ፤ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ ሰብዓዊ ችግሮችን ለመጋፈጥ የሚያስችል “የተለየ አካሄድ መከተል አለብን” ሲሉ ተወያዩ
መንግስት የተመድ ሰራተኞችን ማባረሩን በማውገዝም በአስቸኳይ እንዲመለሱ አሳስበዋል
ተወያዮቹ በግጭቱ ተዋናይ የሆኑ አካላትን በድርድር ወደሚቋጭ ፖለቲካዊ ስምምነት ለማምጣት የተቀናጀ እርምጃ ያስፈልገናል ብለዋል
በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታዎች የሚውል ከ26 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓን አሜሪካ አስታወቀች፡፡
የትግራዩ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በድምሩ 633 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ያስታወቀችው አሜሪካ ከ26 ሚሊዮን ዶላር የሚልቅ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓን ትናንት አስታውቃለች፡፡
ዋሽንግተን ተጨማሪ ድጋፉን ይፋ ያደረገችው ትናንት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን እና የአሜሪካ ህዝብ ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ሰብስበውት በነበረውና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ሁኔታዎች ላይ በመከረው የቡድን ሰባት አባል ሃገራት አስቸኳይ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ነው፡፡
“ሰብዓዊነት አሳስቦኝ እንጂ፤ እንደሚወራው መንግስት ለመቀየር አልመጣሁም”- ሳማንታ ፓወር፣ የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪ
በስብሰባው ዋና ዋና እርጥባንን ጨምሮ የካናዳ፣ የዴንማርክ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የፊንላንድ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የአየር ላንድ፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የኔዘርላንድ፣ የኖርዌይ፣ የስዊድን እና የዩናይትድ ኪንግደም ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
ለ11 ወራት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት በትግራይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ርሃብ እንደተጋለጡ በተመከረበት በዚህ ስብሰባ ተሳታፊዎቹ አሜሪካ እና የእርዳታ አጋሮቿ ችግሮቹን ለመጋፈጥ የሚያስችል የተለዩ የአካሄድ መንገዶችን መከተል አለባቸው ተብሏል፡፡
በትግራይ የእርዳታ መስተጓጎሎችን ለማስቀረት እና በሁሉም ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ድርድር ለማድረግ የተቀናጀ እርምጃን ይፈልጋልም ነው ተሰብሳቢዎቹ ያሉት፡፡
ትናንት ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ጋር በበይነ መረብ ለመከሩት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴገን ኦባሳንጆ ያላቸውን ድጋፍም ገልጸዋል፡፡
የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪዋ ተጨማሪ የሰብዓዊ አገልግሎት መስመር ይከፈት የሚል ጥያቄ አላነሱም- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መላዎችን ይዘይዱ ዘንድ በህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት መወከላቸው ይታወሳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ከሰሞኑ ይሰበሰባል፡፡ ስብሰባው የህብረቱን አባል ሃገራት በማስተባበር በግጭቱ ተዋናይ የሆኑ አካላትን በድርድር ወደሚቋጭ ፖለቲካዊ ስምምነት እንዲመጡ ለማድረግ ያስችላል በሚል መወያየታቸውንም ነው በዩኤስ ኤይድ በኩል የወጣው መግለጫ የሚያትተው፡፡
ተሳብሳቢዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የተቋረጡ የስልክ፣ የባንክ እና የትራንስፖርት ሌሎችንም አገልግሎቶች በአስቸኳይ እንዲያስጀምር አሳስበዋል፡፡
መንግስት “ያልተጠበቀ” ባሉት ሁኔታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ሰራተኞችንና አስተባባሪዎችን ማባረሩን ያወገዙም ሲሆን ውሳኔው በአስቸኳይ እንዲቀለበስ መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡