በሰብዓዊ ጉዳዮች ስም ኢትዮጵያ ጫና እንዲበረታባት አድርገዋል በሚል የሚወቀሱት የተመድ ሰብዓዊ አስተባባሪ ስልጣን ለቀቁ
ማርክ ሎውኩክ በቅርቡ በትግራይ ርሃብ ማጋጠሙን መግለጻቸው የሚታወስ ነው
የ58 ዓመቱ እንግሊዛዊ ኢኮኖሚስት ላለፉት 4 ዓመታት በድርጅቱ ሰብዓዊ አስተባባሪነት አገልግለዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊ እና የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ማስተባበሪያ ሃላፊ ማርክ ሎውኩክ ከስልጣናቸው ለቀቁ፡፡
ሎውኩክ ከስልጣናቸው የለቀቁት ላለፉት 4 ዓመታት የዘለቀው ኃላፊነታቸው ባሳለፍነው አርብ በመጠናቀቁ ምክንያት ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ፍላጎት እያሻቀበ መምጣቱን በኢትዮጵያ ያለውን የትግራይን ሁኔታ እና የየመንን ሁኔታ በማሳያነት በመጥቀስ ያስታወሱት የ58 ዓመቱ እንግሊዛዊ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ (ኢኮኖሚስት) የዓለም ኃያላን ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ካልቻሉ ከዚህም የባሰ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዓለም ሰብዓዊ ስቃዮችን መቀነስ የሚፈልግ ከሆነ ይህንኑ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
ሎውኩክ በእርሳቸው የኃላፊነት ዓመታት ከዓለም ህዝብ አጋማሹ ስር በሰደደ የድህነት አረንቋ ውስጥ ይማቅቅ ነበር ብለዋል፤ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ መናጥ እስከጀመረችበት ጊዜ ድረስ አብዛኛውን ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ለማውጣትና ቁጥሩን ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሎ እንደነበር በመጠቆም፡፡
ሐብታም ሃገራት ደሃ ሃገራትን ሊደግፉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ይህ ካልሆነ ኮሮናን መሰል ወረርሽኞችን፣ ሽብርተኝነትንም ሆነ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡
ለሰብዓዊ እርዳታዎች የሚውለው ድጋፍ ከጥቂት ሃገራትና ተቋማት እንዲሁም እርጥባን የሚገኝ መሆኑ እንደሚያሳስባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
የእርዳታ ሰራተኞችን ያመሰገኑት የሎንደን የምታኔ ሃብት ትምህርት ቤት ምሩቁ ፕሮፌሰር በችግሮች መካከልም ቢሆን ጥረት ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መክረዋል፡፡
ሎውኩክ በትግራይ ክልል ስላለው ሰብዓዊ የአያያዝና የአቅርቦት ሁኔታ ላይ ጠንከር ያሉ ሪፖርቶችን ደጋግመው በማውጣት፤ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡
በቅርቡ እንኳን በክልሉ ርሃብ ማጋጠሙንና 350 ሺ ሰዎች መራባቸውን በመጥቀስ ሪፖርት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም ከግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ በጸጥታው ምክር ቤት ጭምር ሳይቀር ሪፖርት ያደርጋሉ በሚል ጥቂት በማይባሉ ኢትዮጵያውያን ይተቻሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም በክልሉ ያለው የሰብዓዊ እርዳታዎች የአቅርቦትና የተደራሽነት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን በዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጭምር ሳይቀር መመስከሩን በማስታወስ እንዲህ ዓይነቶቹን ሪፖርቶች ውድቅ አድርጓል፡፡
ያልተገቡ ጫናዎችን ለመፍጠር የሚደረጉ የሃሰት ሪፖርቶች ናቸው በማለትም ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጿል፡፡
“በተሳሳተ መረጃ ተመስርተው የሚደረጉ የትኞቹንም ዓይነት ጫናዎች” ኢትዮጵያ እንደማትቀበልም ማስታወቁም የሚታወስ ነው፡፡