አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምትልክ አስታወቀች
ድጋፉ በግንቦት ወር በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈረመው የ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ፓኬጅ አካል ነው ተብሏል
የገንዘብ ድጋፉ በዋናነት ለጤና አጠባበቅ ሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ የሚውል እንደሆነም ተገልጿል
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የዩክሬን “አስፈላጊ አገልግሎቶች” ለማሰቀጠል የሚያስችል 1ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ወደ ዩክሬን እንደሚልክ አስታወቀ።
የግምጃ ቤቱ ጸሐፊ ጃኔት ዬለን በሰጡት መግለጫ “ይህ ለዩክሬን የተደረገው የቅርብ ጊዜ የኢኮኖሚ ዕርዳታ የዩክሬንን ዲሞክራሲ ለመከላከል እየተዋደቀ ያለውን የዩክሬን መንግስት ለመደገፍ የሚደረገውን የፕሬዚዳንት ባይደን ቁርጠኝነት አካል ነው” ብለዋል።
"ይህ እርዳታ የዩክሬን ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለዩክሬን ህዝብ አስፈላጊ አገልግሎቶችን አንዲሰጥ የሚረዳ ነው " ሲሉም አክለዋል፡፡
በግንቦት ወር በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈረመው የ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ፓኬጅ አካል የሆነው ክፍያው፣ በዓለም ባንክ በኩል የሚፈጸም ይሆናልም ነው ያሉት ጃኔት ዬለን።
የገንዘብ ድጋፉ በዋናነት በዩክሬን ውስጥ ወሳኝ ለሆኑ ተግባራት ማለትም ለጤና አጠባበቅ ሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ እንደሚውልም ተገልጿል።
የዓለም ባንክ ግምት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ የዩክሬን ኢኮኖሚ ኩፉኛ ተጎድቷል፡፡
በ2022 እስከ 45 በመቶ እንዲቀንስ ሊቀንስ እንደሚችልም ያለውን ግምት አስታውቋል፡፡
ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በየወሩ በ5 ቢሊዮን ዶላር እያደገ የሚሄደውን የበጀት ጉድለት እያስመዘገበች ያለች ሲሆን ይህ ደግሞ ገንዘቧን ማሰባሰብ ወይም የውጭ ገበያ ፋይናንስ ማግኘት ባለመቻሏ ችግሩ ይበልጥ እየጎላ መሄዱ የዓለም ባንክ ሲያሳስብ መቆየቱም አይዘነጋም፡፡