የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ
ሁለቱ ሀገራት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ 1 ወር ባልሞላው ጊዜ ዉስጥ ነው ሚኒስትሮቹ የተገናኙት
ሚኒስትሮቹ በጀርመን በርሊን ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ
ሁለቱ ሀገራት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብደላህ ቢን ዛይድ ከእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋቢ አሽኬናዚ ጋር ዛሬ ተገናኝተዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን መደበኛ ለማድረግ እና ሰፋ ያለ አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ከተፈራረሙ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሚኒስትሮቹ በጀርመን በርሊን ተገናኝተው በከተማዋ እምብርት የሚገኘውን የአይሁዶች እልቂት መታሰቢያ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡
ሼክ አብዱላሂ በመታሰቢያው ስፍራ በተዘጋጀ የማስታወሻ መጽሐፍ ውስጥ “ከዚህ በኋላ በጭራሽ እንዳይደገም” የሚሉ ቃላትን ጨምሮ ረጅም መልእክት አስፍረዋል፡፡
“ይህ በጣም አስፈላጊ ቦታ የፅንፈኝነት እና የጥላቻ ሰለባ የሆኑ የሰው ልጆች እልቂትን የሚያስታውስ የማይረሳ ቦታ ነው ፣ ይህ ስፍራ በተመሳሳይ ጊዜ አብሮ መኖር ፣ መቻቻል ፣ መተሳሰብ ፣ ሌሎችን ማስተናገድን ፣ የሁሉንም ሃይማኖቶች እና እምነቶች ስለማክበር የሚጠይቁ ክቡር ሰብአዊ እሴቶችን የሚያጎላም ነው” ሲሉም ጽፈዋል፡፡
“አገሬ እነዚህን እሴቶች ተገበረች ፤ ይህም ለእድገቷ ጉዞ ሁል ጊዜም ዋና አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ የሚቆይ ነው” ሲሉም ሼክ አብዱላሂ በማስታወሻው መጽሐፍ ላይ ጽሁፋቸውን አኑረዋል፡፡
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ ማስ ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ በ ሼክ አብደላሂ እና በእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋቢ አሽኬናዚ መካከል የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ግንኙነት አስተናግደዋል፡፡ ሦስቱ ሚኒስትሮች የሀገሮቻቸውን ግንኙነት ለማሳደግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውም በዘ ናሺናል ዘገባ ተገልጿል፡፡
ከውይይቱ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በተለይ ዩኤኢ እና እስራኤል በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ እና ለቀጣናው ደህንነት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከእስራኤል ጋር እያደገ የመጣው ግንኙነት “ዓለም አቀፍ መረጋጋትን ያጠናክራል” የሚል እምነት እንዳላቸው የዩኤኢ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ተናግረዋል ፡፡
“የዛሬው ስብሰባችን በተስፋ የተሞላ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ከእስራኤሉ አቻቸው ጋር በሃይልና በሳይንሳዊ ምርምር ዙሪያ ስለሚኖራቸውው ትብብር እንደመከሩም ገልጸዋል፡፡
ሁለቱም ሚኒስትሮች ስምምነቱ ለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ የመረጋጋት ዘመን የሚያበስር መሆኑን የገለፁ ሲሆን ሼክ አብደላ በአካባቢው መቻቻል እና ብዝሃነት መጠናከር አለባቸው ብለዋል ፡፡